ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የስልጣኔ ባለቤቷ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ይገባል-የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ቆይታችን የተመለከትናቸው የታሪክ፣የስልጣኔና የከተሞቿ የዕድገት ጉዞ አስደንቆናል ሲሉ የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ገለጹ፡፡

የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እና በኤ.ጅ.ኤ ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ አዘጋጅነት ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በዚህ ጉባኤ ላይ ከሰላሳ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ በርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ ከጉባዔው በተጓዳኝ በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች የልማት ስራዎችንና ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ዛሬ ወደ ሀገራቸው መመለስ የጀመሩ ሲሆን፥ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት፣የአፍሪካ ማዕከልነትና የልማት ጉዞዋ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።

ኬንያዊው የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኤልቪስ ሙሺላ፤ ጉባዔው የተለያዩ የአህጉሪቱ ልጆች አንድ ላይ በማሰባሰብ የአፍሪካን ትርክት መቅረጽና ተፅዕኖ መፍጠር ላይ እንድንመክር ያስቻለ ነው ብሏል፡፡

በጉባዔው ስለ አህጉራችን መጻዒ እድል በጋራ በመምከር ትርክት ግንባታን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት የጋራ አቋም እንደተወሰደ ተናግሯል፡፡

ከዚህም ባሻገር እርስ በርስ እንድንተዋወቅ፣ ልምድና ባህል እንድንለዋወጥ አስችሎናል ነው ያለው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚጠሩ ሀገራት አንዷ እንደሚያደርጓት ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ በነበረው ቆይታ የነዋሪዎች ፍቅርና እንግዳ ተቀባይነት እስካሁን ድረስ ካያቸው ሀገራት እጅግ እንደተለየበትና እንዳስደሰተውም ተናግሯል፡፡


 

ከማሊ የመጣው የጉባኤው ተሳታፊ ፋጊወማ ደቦ፤ ኢትዮጵያ የስልጣኔ ሀገር ከመሆኗም በላይ በዕድገቷና በእንግዳ ተቀባይነቷ አስደንቃኛለች ብሏል።

በተለይ አዲስ አበባ በጣም ደስ የምትል ከተማ ሆና አግኝቻታለሁ ነው ያለው።

ከተማዋ ውብ፣ ጽዱ እና ለኑሮ ተስማሚ መሆኗን የጠቀሰው የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪው ፋጊወማ፤ በቀጣይ ስለ አዲስ አበባ እድገትና ጽዳት እንደሚመሰክርና ሰዎች እንዲጎበኟት እንደሚጋብዝ ጠቁሟል፡፡


 

በታሪክ ሲሰማው የነበረውን የኢትዮጵያ ስልጣኔና እድገት አሁን በአካል በመመልከቱ እጅግ መደሰቱን የተናገረው ደግሞ ኬንያዊው ፍራንሲስ ጁማ ነው፡፡

በየትኛውም አጋጣሚ ስለ ኢትዮጵያ መልካምነት በመመስከር ሰዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አምሳደር ሆኘ እሰራለሁ ነው ያለው፡፡


 

ከኮትዲቯር የመጣችው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሳራ ሚሳካ በበኩሏ፤ በአዲስ አበባ ሙዚየሞችን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን ጎብኝተናል ትላለች።

ነዋሪዎቿ በጣም ደጎች ናቸው፤ እንግዳ ተቀባይነታቸውም አስደሳች መሆኑን ተናግራለች።

ኢትዮጵያ የምታስደንቅ ሀገር መሆኗን በማንሳት ብዙ ከተማዎችን መጎብኝቷንና አዲስ አበባ ግን ይበልጥ ልዩና ተወዳጅ ከተማ መሆኗን ጠቅሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም