ቀጥታ፡

ፓርቲው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይበልጥ ይሰራል

ገንዳውኃ/ደብረ ብርሃን ፤ግንቦት 2/2018(ኢዜአ)፡- የብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ  ይበልጥ እንደሚሰራ አስታወቀ። 

የብልጽግና ፓርቲ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ በምዕራብ ጎንደር ዞንና ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር  የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ዛሬ አካሂደዋል። 

የምእራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን  ለማስቀጠል  ሰላማዊና  ፍትሃዊ   ምርጫን  ማካሄድ  ተገቢ ነው።


 

ብልጽግና ፓርቲም ይህንኑ ለመተግበር ለአባላትና ለደጋፊዎቹ ጭምር የምርጫ ስነምግባር ማስተማሩን  ተናግረዋል።

በሰልፉ ላይ የተገኙት የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ  አቶ እንዳላማው ማሩ በበኩላቸው በከተማዋ የተከናወኑ  የኮሪደር፣ የመንገድ፣ የወጣቶች መዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲሁም ሌሎች የልማት ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።

ይህን ለማስቀጠል የሚሆነን ፓርቲ መምረጥ ይገባናል ብለዋል።


 

በተያያዘ ዜና በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ መልእክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳደሩ  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  አቶ በድሉ ውብሸት እንዳሉት እንደ ሀገር የተፈጠረው አካታች የፖለቲካ ምህዳርን  በመጠቀም የብልጽግና ፓርቲ  የፖሊሲ አማራጮቹን  ይዞ ቀርቧል።

የተመዘገበውን  ሀገራዊ እድገት ለማስቀጠል  ፓርቲው ጠንክሮ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኘውን እድል በማስፋት ከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማእከል ለማድረግ የዘንድሮውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በምርጫ ቅስቀሳው ከተሳተፉት መካከል አቶ ዘሪሁን ከበደና  አቶ ዓለማየሁ ሸዋንግዛው እንዳሉት በብልጽግና ፓርቲ የተጀመሩ የሰላምና የልማት ትሩፋቶችን ለማስቀጠል በምርጫው በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም