ትኩረት የተሰጠው የሕጻናት ስነምግብ - ኢዜአ አማርኛ
ትኩረት የተሰጠው የሕጻናት ስነምግብ
በሙሴ መለሰ
በዓለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ሙሉ አካላዊ እና አዕምሯዊ አቅማቸውን ላይ ሳይደርሱ እድሜያቸውን ይቆጥራሉ። የዚህ ልብ ሰባሪ ክስተት መነሻ መቀንጨር (stunting) ይባላል። የስነ ምግብ ባለሙያዎች መቀንጨርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስር የሰደደ ቀውስ ያስከተለ እና የጉዳቱ መጠን የገዘፈ ነገር ግን የአስከፊነቱን ያህል በቂ ትኩረት ያላገኘ ጉዳይ ነው ይሉታል። ብዙ እንደ ግጭቶች እና ሌሎች የዓለም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቀውሶች አርዕስተ ዜና ሲሆን አይታይም። በቀላሉም የህዝብን ትኩረት አይስብም።
ይሁንና የመቀንጨር ጉዳቶች ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ መዘዞች እና የአንድ ሀገር ልማትና ጉዞ ላይ ሊቀለበስ የማይችል ጣጣን ያስከትላል። የህጻናትን ሰውነት ቀስ በቀስ እየጎዳ አዕምሯቸው እና የመፍጠር አቅማቸውን እያደከመ በመሄድ፣ በድምጽ አልባነቱ ውስጥ ውስጡን ዘላቂ መዘዝ እያመጣ ይገኛል። መቀንጨር ህጻናትን በለጋ እድሜያቸው ጊዜ ብቻ ጎድቶ የሚያበቃ ቢሆን መልካም ነበር ዳፋው እስከ ህይወታቸው መጨረሻ የሚከተላቸው ነው። ህጻናት እጅግ በጣም ቁልፍ በሚባለው የእድሜ ክልል ማለትም ከተወለዱ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት ሲገባቸው በምግብ እጦት ምክንያት እድገታቸው አሉታዊ ተጽእኖ ይደርስባቸዋል።
የመቀንጨር ጉዳት አካላዊ ብቻ ጉዳት አድርጎ ማየት የችግሩን ሙሉ ምስል እንደማያሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ይገልጻል። የመቀንጨር ችግር ያለባቸው ህጻናት ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል እንደማይችሉና በሽታ ተጋላጭነታቸው የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ከሚያገኙ ህጻናት ጋር ሲነጻጻር እጅጉን ሰፊ እንደሆነ አመልክቷል። የአዕምሮ እድገት ውስንነት በማምጣት አቅማቸውን በሚገባ አውጥተው እንዳይጠቀሙ ያደርጋል። ህጻናት በምግብ እጦት መቀንጨራቸውን ዩኒሴፍ የህጻናት መብቶች ጥሰት ሲል ይገልጸዋል። ይህም ትውልድ ለአንድ ሀገር የሚኖረው ድርሻ እንዲኮስስ ያደርጋል። መቀንጨር ድምጽ የለውም ኢኮኖሚን በአንድ ጊዜ አያቃውስም ወይንም ህዝብ ላይ ቶሎ ስጋትን አይጭርም ግን ጉዳቱ አያሌ ነው።
በዓለም ላይ ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ ህጻናት መካከል 23 ነጥብ 2 በመቶው የመቀንጨር ሰለባ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ይህ ችግር የህጻናትን አካላዊና አዕምሯዊ አቅም ከመንጠቅ ባለፈ፣ የሀገርን የረጅም ጊዜ እድገት ወደ ኋላ የሚጎትት መዋቅራዊ ሳንካ ሆኖ ቀጥሏል።
በኢትዮጵያ መቀንጨርን ማጥፋት ከምግብ እና ጤና ግቦች በዘለለ ሀገር እንድትበለጽግና እንድታድግ ከሚደረገው ብሄራዊ ውጥን ጋር የተቆራኘ የህልውና ጉዳይ ነው። የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት መሳካት የጀርባ አጥንት ለሆነው አምራች እና ተመራማሪ ሀይል ግንባታ ያለው አስተዋጽዖ ከፍ ያለ መሆኑ ይታመናል።
ምንም እንኳ በሀገራችን የመቀንጨር ምጣኔ እ.አ.አ በ1990ዎቹ ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 39 በመቶ ቢቀንስም፣ አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ያልተወገደ መሆኑ ይታወቃል። ይህንን አስከፊ አዙሪት ለመስበር በ2007 ዓ.ም የሰቆጣ ቃል ኪዳን የተሰኘ ታሪካዊ መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል።
ይህ ታሪካዊ ቃል ኪዳን በ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ውስጥ ሦስት ዋና ዋና የትግበራ ምዕራፎችን አካትቶ የያዘ ነው። የመጀመሪያው የኢኖቬሽን ምዕራፍ (2010-2013 ዓ.ም) በ40 ወረዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማነት ያረጋገጠበት ሲሆን፣ ቀጥሎ የመጣው የማስፋፋት ምዕራፍ (2014-2018 ዓ.ም) የትግበራ ሽፋኑን ወደ 314 ወረዳዎች አሳድጓል። በዚህ ምዕራፍ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህጻናት እና 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን እናቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የመጨረሻው የማስፋት ምዕራፍ (2019 – 2023 ዓ.ም) ደግሞ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር እና ማህበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ መቀንጨርን በኢትዮጵያ ዜሮ ለማድረግ የታለመበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክት መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ ስርዓተ ምግብና ሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ የጤና መድህን፣ የጽዱ ኢትዮጵያ የማስፋፊያ አድቮኬሲና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ የ2018 ዓ.ም የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ በበይነ መረብ ውይይት አካሂደው ነበር።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚ ወቅት የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት መሳካት የጀርባ አጥንት ለሆነው አምራች እና ተመራማሪ ኃይል ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ነበር።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልጸው በዚህም በቃል ኪዳኑ የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ መሰረት የመጨረሻው የአምስት ዓመት የማስፋት ምዕራፍ (2019 – 2023 ዓ.ም) የትግበራ ማስፈፀሚያ እቅድ መጽደቁን ጠቅሰዋል።
በዚህም የመቀንጨርንና ሌሎች የስርዓተ ምግብ ችግሮች ምጣኔን በፍጥነት ለመቀነስ የተገኙ ልምዶች በመቀመር፣ ማህበረሰቡን በባለቤትነት የማሳተፍ ስራን ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስኬታማነት ኢትዮጵያ በዓለም ስርዓተ ምግብ ውስጥ ታሪካዊ አሻራ እንድትጥል ከማድረጉም ባለፈ፣ ጤናማ፣ ምርታማና የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ የሚገነባ ብቁ ትውልድ ለማፍራት ዋስትና የሚሰጥ ነው። ይህ ጉዞ ከመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ባለፈ፣ መላው ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፋቸውን በማጠናከር ለመጪው ትውልድ የገቡትን የህልውና ቃል ኪዳን በተግባር የሚመሰክሩበት ነው።
በአጠቃላይም በአሁኑ ሰዓት የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከልም ሆነ አጠቃላይ ምግብን በዓይነትም ሆነ በጥራት በገበታ ሙሉ ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በመላው ሃገሪቱ እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት በዚህ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ድህነትን ማሸነፍ ሃገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ግቧ የሆነው ሃገራችን በሁሉም መስክ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት የምግብ ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ የዜጎችን ጤንነት በተሟላ መልኩ ማስጠበቅ የሚያስችላትም ነው።