የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለስጋ ምርት የወጪ ንግድ እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው- የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለስጋ ምርት የወጪ ንግድ እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው- የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር
አዲስ አበባ፤ግንቦት 2/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለስጋ ምርት የወጪ ንግድ እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ገለፀ።
በኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወቃል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከልና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለትን መፍታት፣ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስን ዓላማ ያደረገ ነው።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው የዕዳ ተጋላጭነትን በመቀነስ፣ የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግና የፋይናንስ ዘርፉን አካታች፣ ተወዳዳሪና ጤናማ በማድረግ በሀገሪቷ ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባትንም ታሳቢ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ከሊፋ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በውጭ ምንዛሬ የተደረገው ማሻሻያ በዘርፉ ላይ ትልቅ እመርታ አምጥቷል።
ዘርፉ በህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ሲጎዳና ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ በስጋ መዳረሻ ገበያ የተወዳዳሪነት ችግር እንደነበረበት አውስተዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በአቅርቦትና በመዳረሻ ገበያ የነበረውን ችግር መፍታቱን አመልክተው፤ ወደ ውጭ የሚላክ የስጋ ምርት በመጠንና በገቢ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉንም ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ብቻ 87 ሚሊዮን ዶላር ከስጋ ወጪ ንግድ መገኘቱን ገልፀው፤ የእስካሁኑ አፈፃፀም ከአምና በጀት ዓመት የተሻለ የወጪ ንግድ ገቢ እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።
የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የስጋ ምርት መዳረሻ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዋነኛነት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም ሌሎች የአካባቢው ሀገራት እየተላከ መሆኑን ገልጸዋል።
የስጋ ተረፈ ምርት ወደ ቬትናምና ሆንግ ኮንግ እንደሚላክ ጠቅሰው፤ የአፍሪካ አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተከትሎ ወደ ጋና እና ሶማሊያ ምርት እየተላከ እንደሆነም አስረድተዋል።
የአፍሪካ አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን መሠረት በማድረግም የመዳረሻ ገበያን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ከግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቁም እንስሳት አቅርቦት በሚሳለጥበት መንገድ ላይ በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
አዳዲስ መዳረሻዎች ለማስፋት አስፈላጊ በሆኑት በቁም እንስሳት ጤናና የበሽታ ቁጥጥር፣ እርባታና ግብይት ዙሪያ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።