የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2018 (ኢዜአ)፡- በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምልከታ- በሱሉልታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳምንቱ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ በ2 ሺህ 150 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ሰብል ጎብኝተዋል።
መንግሥት በግብርናው ዘርፍ በወሰዳቸው ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች እየተገኙ ያሉ ውጤቶች አመርቂና ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅ መሆናቸውን በጉብኝታቸው ወቅት ተናግረዋል።
መሬት ጦም ማደር የለበትም በሚል ጽኑ እምነት የተጀመረው የበጋ ስንዴ ልማት አስደማሚ ውጤት እያስመዘገበ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ከልመና ራሳችንን መገላገል አለብን፤ ሊታረስና ሊለማ የሚችል መሬት መታረስ አለበት በሚል ጽኑ እምነት የበጋ ስንዴ ልማት መጀመሩን አስታውሰው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አሁን ላይ አስደማሚ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
የቱሪዝም ልማት
የወፍ በረር ጉዟችን የቀጠለ ሲሆን ከሱሉልታ ቀጥታ ወደ አማራ ክልል ባህር ዳር አምርተናል። የባህር ዳር መዳረሻችን በጣና ሐይቅ ደቡባዊ ዳርቻ ላይ በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ይሆናል።
የሪዞርቱ ግንባታ ተጠናቆ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ባሳምንቱ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ገበታ ለሀገር" እቅድ መሰረት በሐይቁ ሌላኛው አቅጣጫ ከሚገኘው የጎርጎራ ብርሃን (ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት) ጋር በመቀናጀት የጣናን የቱሪዝም ቀጣና ለማነቃቃት አላማ በማድረግ ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት መገንባቱ ተመላክቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህርዳር ከተማ ቆይታቸው በ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚገነባውን ፎር ፖይንትስ ባይ ሸራተን ጣና የሆቴል ፕሮጀክት ግንባታም አስጀምረዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት የሚገነባው ይህ ዓለም አቀፍ ሆቴልም በ18 ወራት ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል።
የመልካ ቁንጡሬ ሁነት
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀንን በዩኔስኮ በተመዘገበው በመልካ ቁንጡሬ–ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ መካነ ቅርስ ስፍራ በሳምንቱ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የቅርስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ በመልካ ቁንጡሬ–ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ መካነ ቅርስ ስፍራ ተከብሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ፤ ባህላዊና የተፈጥሮ ቅርሶች ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ይቀጥላሉ ብለዋል።
ሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ
የሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ልማት የዲዛይን ሥራ ተጠናቅቆ ለህዝብ ይፋ የተደረገውም በዚሁ ሳምንት ነው።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ እንደገለጹት ከተማዋን ለኑሮ፣ ለስራ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው።
የልማት ስራዎቹ ከተማዋ ሀገር አቀፍ ስብሰባዎችን¸፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎች ኩነቶችን በማስተናገድ ተመራጭ እየሆነች እንድትመጣ አድርገዋታል ብለዋል።
የሀይቅ ዳርቻ ልማቱ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትና የተወዳዳሪነት አቅም ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ጠቁመው ለተግባራዊነቱ በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ ብለዋል።
የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻን በማልማትና ከአካባቢው መስህቦች ጋር በማስተሳሳር ሀይቁን የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።
ጅማ ዞን ጎማ ሁለት
በጅማ አጠር ያለ ቆይታችን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጅማ ዞን ጎማ ሁለት የምርጫ ክልል የብልጽግና ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸውን በማስተዋወቅ የቅስቀሳ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በዚህ የቅስቀሳ ስነ ስርአት ላይ የፓርቲው አባላትና አመራሮች እንዲሁም ደጋፊዎች በመውጣት የተሳተፉበት መሆኑን ለማየት ችለናል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነመራ ቡሊ፤ በፓርቲው አመራር ሰጪነት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ርዕሰ መስተዳድሩ በሚወዳደሩበት ምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳና እጩ የማስተዋወቅ መርሐ ግብር የተካሄደውም በዚሁ ሳምንት ነበር።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት ብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችንን ሲያከናውን ቆይቷል።
በባለፉት የለውጥ ዓመታት የሀገርን እድገትና የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የሽንሌ እመርታ
በሳምንቱ በሶማሌ ክልል ሽንሌ ወረዳ የተገነባው የ10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት መንገድና በሽንሌ ጠቅላላ ሆስፒታል የተገነባው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተመርቋል።
በሽንሌ ወረዳ የመርማርሳ ከተማን ከድሬዳዋ ጋር የሚያስተሳስር የ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታንም አስጀምረዋል።
የተገነቡት የልማት ስራዎች በተለይም ለወረዳው እመርታ መሆኑን የገለጹት አመራሮቹ በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት የማልማትና የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።
ሳተላይት
በሐረር የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀቢያ ጣቢያ ተከላ ስራ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በተገኙበት በዚሁ ሳምንት ተጀምሯል።
የሳተላይት የመገኛ መረጃ መቀበያ ጣቢያው በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን የመረጃ ግብዓት ከመሆን አኳያም ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተመላክቷል።
የመንገድ ዲዛይን፣ አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ስራ ለሚያከናውኑ፣ የመሬት አጠቃቀምን በጥንቃቄ ለመቆጣጠር፣ ለይዞታ መረጋገጫና ሌሎችም የተሟላ መረጃ ለመስጠት የሚጠቅም መሆኑ ታውቋል።