ባለፉት አምስት ዓመታት ሴቶችን አስተማማኝ የብልፅግና አቅም መገለጫ ማድረግ ተችሏል - አቶ ሞገስ ባልቻ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አምስት ዓመታት ሴቶችን አስተማማኝ የብልፅግና አቅም መገለጫ ማድረግ ተችሏል - አቶ ሞገስ ባልቻ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 2/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት ሴቶችን አስተማማኝ የብልፅግና አቅም መገለጫ ማድረግ መቻሉን በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ።
ይህን የገለጹት የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበትን የምርጫ ቅስቀሳ ንቅናቄ ባካሄደበት ወቅት ነው።
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የፓርቲው ዕጩዎችና ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ደጋፊዎች ታድመዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ የመደመር እሳቤ ዋናው መርህ ሁሉንም አቅሞች አቀናጅቶ ለሀገር ግንባታ መጠቀም መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም መሰረት ባለፉት አምስት ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በስኬት ተከናውነዋል ብለዋል።
ሴቶች በብልፅግና ጉዞ ውስጥ ወሳኝና አይተኬ አቅም መሆናቸውን ፓርቲው በፅኑ ያምናል ያሉት አቶ ሞገስ ሴቶች ቁልፍ በሆኑ የመንግስት ተቋማት ውስጥ እንዲመደቡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ የመጣ ሲሆን፣ በተሰጣቸው ኃላፊነትም አንጸባራቂ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
እነዚህ ስኬቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የቀረቡ ሳይሆኑ ብልፅግና በተግባር ሰርቶ ያሳያቸውና የሴቶችን ሕይወት የለወጡ እውነታዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ ለሴቶች ተጠቃሚነት የተሰሩ ዓበይት ተግባራትና የተገኙ ድሎች በሰፊው ተስተጋብተዋል።