የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2 /2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ በአበበ በቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወደ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ የወረደው አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ልደታ ክፍለ ከተማ በ19 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሊጉ ደካማ አቋም ያሳየው አርባምንጭ ከተማ ባለፉት 17 የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። በውድድር ዓመቱ ያሸነፋቸው ጨዋታዎች ብዛት ሁለት ብቻ ናቸው።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ልደታ ክፍለ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ይርጋ ጨፌ ቡና ከሲዳማ ቡና በአበበ በቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ይርጋ ጨፌ ቡና በ17 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በ34 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
በ24ኛ ሳምንት ልደታ ክፍለ ከተማን 2 ለ 0 ያሸነፈው ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።
አዲስ አበባ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በ11 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ከተሸነፈ ወደ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ይወርዳል።
በ24ኛ ሳምንት በመቻል 3 ለ 2 የተሸነፈው ባህር ዳር ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጨረሻ ሳምንት የሆነው የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከ25ኛ ሳምንት በፊት አስቀድሞ እንደሚደረግ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
የመርሐ ግብሩ ቅያሬ ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የተገናኘ መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ63 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 63 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰሎሞን በ24 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ይገኛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ ደግሞ በ20 ግቦች ተከታዩን ስፍራ ይዛለች።