ባሳለፍነው ሣምንት ... - ኢዜአ አማርኛ
ባሳለፍነው ሣምንት ...
ከሚያዝያ 25 እስከ ግንቦት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …
· ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ባሳለፍነው ሳምንት የተከፈተ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ውጤት ተኮር አመራራችን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ተንጸባርቋል ብለዋል። የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት ዐቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ በማድረግ፣ ባለፉት አራት ዓመታት ከ2 ሺህ 800 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ተችሏል ብለዋል።
ኤክስፖው ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ንቁ አምራቾችን እና ስታርትአፖችን በጨመረ ዐቅም በአንድነት ማሰባሰቡን ጠቁመው፤ በጋራ በመሆን ይህንን ጠንካራ መነቃቃት በማስቀጠል ለሚመጣው ትውልድ ጽኑ፣ በኢንዱስትሪ የበለጸገች እና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እንገነባለን ብለዋል።
· 85ኛው የጀግኖች ዓርበኞች በዓል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለ85ኛው የጀግኖች ዓርበኞች በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ ሚያዝያ 27 ቀን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ዓርበኞች የፋሽስትን ወረራ የቀለበሱበትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስከበሩበት በዓል መሆኑን አውስተዋል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ብሔራዊ ዓርበኞችን ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የራስ ፍላጎትን፣ ባንዳነትን እና ወራሪን እምቢ የሚል ዓርበኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢንዱስትሪ ዓርበኞች፣ የግብርና ዓርበኞች፣ የጸጥታ ዓርበኞች፣ የፖለቲካ ዓርበኞች፣ የንግድ ዓርበኞች፣ የዲፕሎማሲ ዓርበኞች፣ የመንግሥት አገልጋይ ዓርበኞች፣ የሕክምና ዓርበኞች፣ የትምህርት ዓርበኞች፣ ወዘተ. . . ያስፈልጉናል ሲሉም አብራርተዋል።
ይህን በዓል የምናከብረው የየራሳችንን የዓርበኝነት ደረጃ በመገምገም ነው፤ በዚህም መሠረት ለኢትዮጵያ ምን ያህል ዓርበኞች ነን? ማለት ይገባናል ብለዋል በመልዕክታቸው።
በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ዓርበኞቻችን ታሪክ የሠሩት የውስጥ ባንዳንና የውጭ ባዳን ድል ነሥተው ነው፤ እኛም የአባቶቻችን ልጆች በመሆናችን አሁንም ያንን ድል እንደግመዋለን ብለዋል።
ዛሬ የዓርበኝነት ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ሆኗል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዚህ ዘመን ዓርበኝነት በሥራ መትጋትና በዕውቀት መመራት፣ የድህነትን ታሪክ ለመቀየር ቆርጦ መነሣት፣ የተሻለች የነገዋ ኢትዮጵያን በላባችን መገንባት ነው ሲሉም አስረድተዋል። ስለሆነም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በዲፕሎማሲ መስኮች ድልን እያስቀጠልን፤ በተደመረ ዐቅም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ የሚያወጣ የዘመኑ ዓርበኛ ልንሆን ይገባል ነው ያሉት።
· የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱልልታ ወረዳ በ2 ሺህ 150 ሔክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ማሳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት የጎበኙ ሲሆን በወቅቱም፤ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የጀመርነው ጥረት በላቀ ውጤት ቀጥሏል ብለዋል።
· የኢትዮጵያና አዘርባጃን ግንኙነት በይበልጥ መጠናከር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ከኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብ ጄተን ጋር ውጤታማ የሥልክ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መመክራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በተለያዩ ዘርፎች ያለንን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ሐሳብ ተለዋውጠናል ብለዋል።
·የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት፤ የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ በሚል መሪ ሐሳብ ባለፉት ዓመታት በሚዲያ ዘርፍና ተቋማት ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች የቀረቡበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅትም፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት የሚዲያ ምኅዳሩን በዴሞክራሲያዊ ዐውድ ለመዋጀት በወሰድነው እርምጃ ለሀገር ግንባታ የሚረዳ መሠረት ተጥሏል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህ ውጤት እንዲቀጥልም ሚዲያዎች ከዋልታ ረገጥነትና ከጽንፈኝነት ወጥተው በእውነት ላይ የተመሠረተ ትርክት በመገንባት፣ ለጋራ ማንነትና ለብሔራዊ መግባባት በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚዲያዎቻችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በጥናት የታገዘ ጥልቅ ትንተና በማቅረብ፣ ከአርዕስት ሽያጭ ባለፈ ለሀገር አጀንዳዎች ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።
ተግባራቸውም በዓላማ፣ በዕይታ፣ በሙያዊ ብቃትና ለሕዝብ ቅርብ በመሆን ላይ ተመስርቶ፣ ሚዛናዊነትን በጠበቀ መልኩ ለሀገር ብልጽግና መንገድ ጠራጊና ችግር ፈቺ ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
· ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጂቡቲው ፕሬዚዳንት በዓለ ሢመት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በተመራጩ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በዓለ ሢመት ሥነ-ሥርዓት ለመታደም ወደ ጅቡቲ አቅንተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ለሀገራቸው የሚሰጡት አገልግሎት ሁለንተናዊ እድገትን እንዲያስቀጥል ልባዊ ደስታዬንና መልካም ምኞቴን ልገልጽ እወዳለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ መካከል ያለው የቆየ ወዳጅነት እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለሕዝቦቻችን የጋራ ብልጽግና እንዲሁም ለቀጣናችን ሰላምና መረጋጋት መጠናከር መሰረት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
· የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት መመረቅ
ሪዞርቱ ባሳለፍነው ሳምንት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመረቀ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅትም ለባሕር ዳርና ለአካባቢው ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት መንግሥት ለቱሪዝም መዳረሻዎች የሰጠው ትኩረት ምን ውጤት እንዳመጣ በገሐድ የሚነበብበት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ የአካባቢውን የቱሪዝም መሥመርና ሠንሠለት የሚያጠናክር ማረፊያና መዳረሻ ነው ብለዋል። ሪዞርቱ ዘመናዊ እና ቅንጡ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ሱቆች፣ አምፊ ቴአትር እና መሰል መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ ጣናን ተንተርሶ የተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ Four Points by Sheraton ሆቴል የግንባታ ፕሮጀክት በይፋ አስጀምረዋል።
በርካታ አገልግሎቶችን አሟልቶ በ18 ወራት ግንባታው የሚጠናቀቀው ይህ ሆቴልም የግል ባለ ሀብቱ በሀገራችን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን ሚና የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች እያመጣ ያለውን ለውጥ አድንቀው፤ ይህ የሆቴል ግንባታም ለባሕር ዳር በጸጋ ላይ ጸጋ የሚጨምር መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ማጠቃለያ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባሰላፍነው ሳምንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአራተኛው የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ማጠቃለያ ላይ የተመለከትናቸው የጥራትና የፈጠራ ውጤቶች የሀገራችንን የማምረት ዐቅም የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ታምርት የሉዓላዊነታችን መሠረት የብልጽግናችን ምሦሶ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እያሳየችው ያለው ተጨባጭ ዕድገት የብልጽግናችን ማብሠሪያ እየሆነ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት በምልዓት የሚረጋገጠው በምርት ራስን በመቻል መሆኑን በመገንዘብ የተጀመረው ይህ ንቅናቄ፤ ተኪ ምርትን በማሳደግ፣ የፋብሪካዎችን ዐቅም በመገንባት እና የሥራ ባህልን በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።
መንግሥት ለዘርፉ ምቹ ፖሊሲዎችንና ድጋፎችን ማመቻቸቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ ቀጣዩን ኤክስፖ ይበልጥ በፈጠራና በስብጥር የላቀ ለማድረግ እንሠራለን ሲሉ አመላክተዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ባሳለፍነው_ሳምንት #ኢዜአ