የኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቡና እና መቻል ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና እና መቻል አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቢንያም ጌታቸው በ16ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ኢትዮጵያ ቡና መሪ መሆን ችሏል።
ብዙም ሳይቆይ ብሩክ ማርቆስ በ21ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፈው ጎል መቻል አቻ ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ43 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ቡናማዎቹ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፉም።
መቻል በ49 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ31ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ምድረ ገነት ሽሬን 4 ለ 0 ሲረታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መቀሌ 70 እንደርታን፣ ሀዱያ ሆሳዕና ሃዋሳ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።