ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመፈጸም የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት እያበሰረች ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በመፈጸም የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት እያበሰረች መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ የካ፣ ቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሕንፃዎችን መርቀዋል።


 

ከንቲባ አዳነች በሥነ-ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያን ብልፅግና በማረጋገጥ የሀገረ መንግስት ግንባታ የሚጠናከርባቸው እና ጀምሮ የማጠናቀቅ ልምምድ ዕድገት ወሳኝ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ዓመታት ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር በሁሉም መስክ አመርቂ የልማት ውጤቶች የተመዘገቡባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተያዘው ግብ መሠረት በመዲናዋ በሁሉም መስክ ስምና ገፅታዋን የሚመጥን የልማት ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በተግባር የሚለካ አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን አንድነትና የጋራ ትርክት በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት እያበሰረች የምትገኝ ከተማ ናት ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ይህም ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ተምሳሌትና የስበት አካል እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሕንፃዎችም ከተቋም ግንባታ ባሻገር የጋራ ትርክት በማስረፅ ሕብረብሔራዊ አንድነት የሚጎለብትባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

የሕንፃዎቹ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ ግዙፍና የልማት አቅም የሆኑ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የማጠናቀቅ ልምምድ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንም የሀገርን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ለሚተጋውና የምርጫ ምልክቱን የስንዴ ነዶ ላደረገው የብልፅግና ፓርቲ ድምፅ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አባል መኩርያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ፓርቲው ግልፅ የልማት ፍኖተ ካርታ በመቅረፅ በአዲስ አበባ እና በመላ ሀገሪቱ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም