ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የግብርና ምርምሮችን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የግብርና ምርምሮችን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ
ሐረር፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረጉ ምርምሮችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ምሁራን አመላከቱ።
የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት፣ በሰው ጤና እና በቱሪዝም ዘርፎች ላይ የሚያስከትላቸውን ተግዳሮች በቴክኖሎጂ ታግዞ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ዓለምአቀፍ ኮንፍረንስ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በኮንፈረሱ ዘመናዊ ግብርናን ለማስፋፋትና ማኅበረሰባዊ ችግሮችን በፈጠራ ታግዞ ለመፍታት በዳታ ሳይንስ የታገዘ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።
በኢትዮዽያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ዳይሬክተር ደጀኔ ግርማ (ዶ/ር) የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ባደረገ የግብርና ምርምር ሥራዎች ማስደገፍ ይገባል ብለዋል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ የተለያዩ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የምርምር ሥራዎችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ተናገረዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዚዳንት ይስሃቅ ዩስፍ (ዶ/ር) የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን በቴክኖሎጂ በታገዘ ምርምር በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ዲጂታል ቴክኖሊጂንና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ የሰሜኑ ክፍል መሆኑንና ችግሩን አስቀድሞ በምርምር በመፍታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ተገቢ ነው ያሉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) ናቸው።
ኮንፍረንሱ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት፣ በሰው ጤና እና በቱሪዝም ላይ የሚያስከትለውን ተግዳሮት በቴክኖሎጂ ታግዞ መፍታት በሚቻልበት ላይ አተኩሮ መካሄዱን የገለጹት ደግሞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) ናቸው።
ተመራማሪዎችና ምሁራን አበርክቷቸውን እንዲያጎለብቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዞ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የጤና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል
ለሁለት ቀናት በተካሄደው ኮንፍረንስ ተመራማሪዎች፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የፌዴራልና የክልል ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላትና ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የምርምር ውጤቶችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።