በጠቅላላ ምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ሴቶች በጠቅላላ ምርጫው ያላቸውን ተሳትፎና የወሳኝነት ሚና ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌደሬሽኑ በምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች በምርጫ ታዛቢነት ለሚሳተፉ ሴቶች የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፌደሬሽኑ በመላው አገሪቱ በተለያዩ አደረጃጀቶች የታቀፉ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባላቱ በምርጫው ያላቸውን ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ለማሳደግ እየሰራ ነው።
ሴቶች በመራጭነት፣ በተመራጭነት እና በታዛቢነት ያላቸውን ሚና ለማጎልበትም አቅማቸውን የማሳደግና የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ የሚያበረክተውን የላቀ አስተዋጽኦ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሴቶች በተለያየ መንገድ እንዲገነዘቡ ከማድረግ ባለፈ የማነቃቃት ሥራ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
ዛሬ በድሬዳዋ የተጀመረው የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የምርጫ ታዛቢዎች የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ ሴቶች በምርጫው የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያስችላል ሲሉም አክለዋል።
የፌደሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ትዕግስት ተረፈ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሴቶችን ተሳትፎ የማላቅ ሥራ እየተሰራ ነው።
ምርጫው ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች ገለልተኛ ሆነው ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል።
ለሁለት ቀናት እየተሰጠ ያለው የአሰልጣኞች ስልጠናም በጠቅላላ ምርጫው ሴቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታዛቢነት መብትና ግዴታ እንዲሁም ታዛቢዎች ሊከተሏቸው በሚገቡ የስነምግባር ድንጋጌዎችና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
ስልጠናውን እየተከታተሉ ያሉት ሴት የምርጫ ታዛቢዎች ከድሬዳዋ አስተዳደር፣ ከሶማሌ እና ከሐረሪ ክልሎች የተወጣጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ በመላው አገሪቱ 10 ሺህ የምርጫ ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራ ለማወቅ ተችሏል።