ቀጥታ፡

የመረጃ ስርዓቱ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመከተል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው

ሰመራ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ብሔራዊ የግጦሽ መሬት የጤና ክትትል የመረጃ ስርዓት ሳይንሳዊ መንገዶችን በመከተል አርብቶ አደሩን እና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ተግባራዊ የሚደረግ ብሔራዊ የግጦሽ መሬት የጤና ክትትል የመረጃ ስርዓት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ዛሬ በሰመራ ተካሄዷል። 

በመድረኩም ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዑመር ኑሩ እንደገለፁት፤ በክልሉ የአርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ።


 

የአርብቶ አደሩ ህይወት ከእንስሳት ሀብቱና ከግጦሽ መሬቱ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን አውስተው የመረጃ ስርዓቱ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመከተል አርብቶ አደሩን እና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የመረጃ ስርዓቱ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመሬት መራቆትና በመጤ አረሞች ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት መሬት መፍትሄን ይዞ የመጣ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል።

በተለይም የአዋሽ ወንዝን ተከትሎ በርካታ አካባቢዎች በመጤ አረም በመወረራቸው ሳቢያ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለመቅረፍም ሳይንሳዊ ዘዴን በመጠቀም ጥረት መደረጉ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ያሳድገዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የእንስሳትና ንግድ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዮሴፍ መካሻ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የመረጃ ስርዓቱ በተለይም ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለትምህርት ተቋማትና ሌሎች አካላት መረጃ በመስጠት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ እገዛ እንደሚያደርግም አክለዋል።

ስርዓቱ ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ለግጦሽ የሚውሉ ስፍራዎችን በመለየት፣ የተራቆቱና ጉዳት የደረሰባቸው እንዲታወቁ አስፈላጊውን መረጃ በማድረስ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ናቸው።


 

ይህም በክልሉ ያለውን የዘርፉን አቅምና ክፍተት በመለየት ለምርታማነት መጨመር ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም