ሀገራዊ ምክክሩ የትውልድን የተሻለ መፃኢ እጣ ፋንታ የሚወስን ወሳኝ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የትውልድን የተሻለ መፃኢ እጣ ፋንታ የሚወስን ወሳኝ መድረክ ነው
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የትውልድን የተሻለ መፃኢ እጣ ፋንታ የሚወስን ወሳኝ የጋራ መድረክ መሆኑ ተገለጸ።
ወጣቶች በሀገራዊ ምክክር ዋና ጉባኤ ሀገራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ የልዩነት ሃሳቦችን በምክክር በመፍታት በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል።
በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አደረጃጀቶች የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሥራ በስኬት ተጠናቋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ማጠናቀቁን ተከትሎ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የመጨረሻ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን በማስፈን ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ መድረክ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የፈጠረውን ዕድልም በታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና መሰል ጉዳዮች በሚስተዋሉ ዋና ዋና ሀገራዊ የሃሳብ ልዩነቶች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽነር ማርቆስ ማቲዎስ፤ ሀገራዊ ምክክር ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንቢያ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሀገራዊ ምክክር የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም የኢትዮጵያን መፃኢ እጣፋንታ የተሻለ ለማድረግ በትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሱልጣን አሊ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የትውልድን መፃኢ እጣ ፋንታ የሚወስን ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።
በዚህም በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ሂደት ወጣቶች ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት ወጣቶች ገንቢ ሚና እንዲወጡ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ወጣቶች ማኅበር አባል በቃሉ መሰረት፤ በክልሉ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች ላይ በንቃት መሳተፋቸውን አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም በዜጎች መካከል ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጿል።
በቀጣይም ዋናውን ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ ሂደት ገንቢ ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።