ቀጥታ፡

በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ  

ቆሼ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳውን በማረቆ ልዩ ወረዳ ቆሼ ከተማ አካሂዷል።


 

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በፓርቲው በመደመር እሳቤ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተጀመረውን የብልጽግናና የማንሰራራት ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲውና በሌሎች መስኮች በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ስኬቶች ማስመዝገብ ስለመቻሉም አመልክተዋል።

ፓርቲው አስተሳሳሪ ትርክትን በመገንባት፣ በአካባቢው ሰላምን በማጠናከርና በሁሉም ዘርፍ ውጤታማነትን በማሳደግ  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደገ መምጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ በፓርቲው መሪነት የማህበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡


 

የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ በበኩላቸው፤ በለውጡ መንግስት የልዩ ወረዳው ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር የዘመናት ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ ከልማት ትሩፋት ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት ብለዋል። 

በቅስቀሳ መርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን እና የልዩ ወረዳው ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም