በዞኑ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተከናወኑ ነው
ገንዳ ውኃ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
አስተዳደሩ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከተሰኘ አጋር አካል ከ27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁስና የመማሪያ ክፍል ግንባታ ርክክብ ዛሬ በገንዳ ውሃ ከተማ አካሄዷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ በዞኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ቁልፍ ተግባር ሆኖ እየተከናወነ ይገኛል።
በትምህርት ዘርፉ የሚደረጉ ድጋፎች የነገውን ትውልድ ግንባታ ታሳቢ ያደረገ እገዛ በመሆኑ የሚደነቅና ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው ብለዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አያና በበኩላቸው፤ የትምህርት ተቋማትን ተደራሽነት በማሳደግና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመማር ማስተማር ስራውን የተሳለጠ በማድረግ በኩል ባለፉት ጊዜያት በትብብር የተሰሩ ስራዎች ውጤት የታየባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የነበረውን ችግር የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል።
ለመማር ማስተማር ስራው ውጤታማነት እየተደረጉ ያሉ የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያረጋገጡት ደግሞ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የመተማ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ማርቆስ ሞላ ናቸው።
ድጋፉም ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር፣ የፈተና ወረቀት ማባዣ ሪዞ ማሽን፣ አዲስ የተገነቡ አራት የመማሪያ ክፍሎችና ሙሉ ጥገና የተደረገላቸው ሁለት ብሎኮችን ያካተተ ነው።
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የዞኑ አመራሮች፣ የድርጅቱ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።