ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በተግባር የሚለካ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በተግባር የሚለካ ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስድስት ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሕንፃዎችን መርቀዋል።


 

በዚሁ ወቅት እንዳሉትም፤ ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሕንፃዎች የጋራ ትርክት በማስረፅ ሕብረብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርባቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ ብልፅግና በማረጋገጥ የሀገረ መንግስት ግንባታ የሚጠናከርባቸውና ጀምሮ የማጠናቀቅ ልምምድ ዕድገት ወሳኝ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ዓመታት ፈተናን ወደ ድል በመቀየር በሁሉም መስክ አመርቂ የልማት ውጤቶች የተመዘገቡባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተያዘው ግብ መሠረትም በመዲናዋ በሁሉም መስክ ስምና ገፅታዋን የሚመጥን የልማት ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶችም የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በተግባር የሚለካ አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ህብረብሄራዊ አንድነትና የጋራ ትርክት በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም