ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ

ወልቂጤ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ በጉራጌ ዞን የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ተናገሩ።

በወልቂጤ ከተማ በጉብሬ ክፍለ ከተማ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይም አቶ ላጫ ጋሩማ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቶቹ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ናቸው።


 

ከፕሮጀክቶቹ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ግንባታ፣ የፍርድ ቤት ህንፃ እና የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታዎች ተጠቃሽ እንደሆኑ ገልጸው ህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላሉ ብለዋል።

በመሆኑም መሰል የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው፤ በከተማው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

በተለይም የህዝብን ጥያቄ የሚመልሱ እና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል።

በወልቂጤ ከተማ የጉብሬ ክፍለ ከተማ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበሩት እነዚህ ፕሮጀክቶች ብቻ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው መመረቃቸውን ተናግረዋል።

የተገነባው የማህበረሰብ አቀፍ  መድኃኒት ቤትም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ወርቅነሽ ወልዴ፤''በከተማችን በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱ የተረጋገጠ መድኃኒት እንድናገኝ መደረጉ ለህብረተሰቡ ጤና ትኩረት መሰጠቱን የሚያሳይ ነው'' ብለዋል፡፡


 

ሌላኛው የከተማው  ነዋሪ አቶ ዚያድ በደዊ ከግል መድኃኒት ቤቶች በከፍተኛ ዋጋ መድሃኒት ይገዙ እንደነበር ጠቅሰው በቅርበት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ጠቅሰዋል።


 

በቅርበት የክልሉ ምድብ ችሎት ተከፍቶ መስራቱ ችግራቸውን እንደሚያቀልላቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ አብዲ አሺቅ ናቸው።

ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁ መሰረተ ልማቶች የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም