ቀጥታ፡

የደሴ ከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት መምሪያ ውጤታማ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግርና የእውቅና ስነ-ስርዓት

ደሴ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ የደሴ ከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት መምሪያ ውጤታማ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግርና የእውቅና ስነ-ስርዓት ማካሄዱን አስታወቀ።

በመድረኩ ላይ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለፁት፤ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅና ልማትን በማፋጠን ረገድ በትኩረት ተሰርቷል።

ይህም የከተማዋን ፀጋ በማልማት ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ውጤታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በተደረገው ድጋፍም ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግር በማድረግ ወደ በላቀ ሁኔታ ተግባራቸውን ለመወጣት እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱልሃሚድ ይመር በበኩላቸው፣ በዛሬው እለትም ስምንት ኢንተርፕራይዞች ወደ ባለሃብትነት እንዲሸጋገሩ መደረጉን አስረድተዋል።

በተጨማሪም 20 ኢንተርፕራይዞች ባሳዩት የተሻለ የስራ አፈጻጸም እውቅና እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመው ይህም በቀጣይ ውጤታማነታቸውን በማስቀጠል ወደ ባለሃብትነት ለማሸጋገር ያለመ ነው ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞቹም ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ካፒታል በማስመዝገባቸውና በስራቸው በቀጠሩት የሰው ሃይል ተመዝነው መሆኑን አመልክተዋል።

የደረጃ ሽግግር ላደረጉ ኢንተርፕይዞች የቦታና የብድር አቅርቦት በማድረግ ፈጥነው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አስረድተዋል። 

መቅደስና ጓደኞቿ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ማህበር አስተባባሪ መቅደስ መሰለ እንደገለጸችው፣ በ10 ሺህ ብር ካፒታል የጀመረችው ስራ አሁን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማድረስ መቻሏን አስረድታለች።

ካፒታሏን ማሳደግ የቻለችውም የተለያዩ ቦርሳዎችን፣ ቀበቶዎችንና ሌሎች የቆዳ ምርቶችን በማምረትና በመሸጥ መሆኑን ጠቁማ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሏን ገልጻለች።

በብረታ ብረት ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት አብዱራህማን እንድሪስ በሰጠው አስተያየት በተሰማራበት ዘርፍ ፋብሪካዎችና ማሽኖች ግብዓት በማምረት ለውጤት መብቃቱን ተናግሯል።

በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ23 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም