ቀጥታ፡

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን በማጠናከር የታለመውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ይሰራል

ጋምቤላ፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን በማጠናከር የታለመውን ብልጽግና እውን ለማድረግ እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

ፓርቲው "ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ አባላቱና ደጋፊዎቹ በተገኙበት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በመደመር እሳቤ ባለፉት ዓመታት እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ድሎች ተመዝግበዋል።


 

ባለፉት ዓመታት ፓርቲው ለህዝብ በገበው ቃል መሰረት በተለይ ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት በኩል ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲው የህዝብ ይሁንታ ካገኘ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የታለመውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ፓርቲው በመደመር እሳቤ በህዝቦች መካከል ያለውን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ አበክሮ እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት።


 

ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር ላቀዳቸው የልማት ግቦች መሳካት ህዝቡ ከፓርቲው ጎን በመሆን በጠቅላላ ምርጫው ይሁንታውን እንዲሰጠውም ጥሪ አቅርበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሽኔ አስቲን በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት እውን ለማድረግ ያለመታከት እየሰራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በየአካባቢው የሚገኙ ጸጋዎችን ካለው የሰው ኃይል ጋር አቀናጅቶ ባከናወናቸው የልማት ሥራዎች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም