ቀጥታ፡

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በሕዝብ ይሁንታ ድምጽ ለማግኘት ዝግጅት አድርጓል - የፓርቲው ፕሬዝዳንት አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በመጪው ሀገራዊ ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ ድምጽ ለማግኘት ዝግጅት ማድረጉን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) ገልጹ።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ያለውን አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች ለህዝብ ለማስተዋወቅ የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል።

ፓርቲው ባካሄደው የቅስቀሳ መርሃ ግብር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች የያዛቸውን አዳዲስ አማራጭ ዕቅዶች ለደጋፊዎቹና ለነዋሪው አቅርቧል።

የፓርቲው ፕሬዚዳንት አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) በወቅቱ፤ ፓርቲያቸው ተፎካክሮ መንግስት መሆን የሚያስችለውን ድምጽ ለማግኘት ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲው ‎የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ባለፉት ቀናት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ዓላማውን ለህዝብ ሲያስተዋውቅ መቆየቱን ተናግረዋል።

የዛሬው የአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ቅስቀሳ ፓርቲው ያለውን የፖሊሲ አማራጭ ለነዋሪው በቀጥታ ለማድረስና የምረጡኝ ጥሪ ለማቅረብ የታለመ ነው ብለዋል።

‎በሀገሪቱ እየተገነባ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት ለማጠናከር የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሳቀሳቸውና ሃሳባቸውን ለህዝብ ማቅረባቸው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የዛሬው መርሃ ግብርም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲው የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።




‎የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው የምርጫ ምልክቱ ብዕር ማድረጉንና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖሊሲ አዘጋጅቷል ብለዋል።

ፓርቲው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች ፖሊሲውን በተለያዩ መንገዶች እያስተዋወቀ መሆኑን አመልክተዋል።

ፓርቲው የተፈጠረውን ምቹ የምርጫ ሁኔታ በመጠቀምና በተለያዩ መንገዶች ለደጋፊዎቹና ለመላው የሀገሪቱ ሕዝቦች አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦቹን እያስተዋወቀ መሆኑን የገለጹት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አዲስ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም