ቀጥታ፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት የሚጠበቅበትን ሚና ይወጣል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እንደሚወጣ የፓርቲው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት፣ በሀገራዊና ቀጣናዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

መድረኩን አስመልክቶ የፓርቲው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሀገር ዘላቂ ልማትና ሰላም የፓርቲው ቀዳሚ አጀንዳዎች ናቸው ብለዋል።

የአንድ ሀገር ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነትም ዘላቂ ልማትና ሰላምን በማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያፀና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በ7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኅን አማራጮችን በመጠቀም የፖሊሲ አማራጫቸውን እያስተዋወቁ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በመድረኩም በምርጫ ዝግጅት ምዕራፍ የፖሊሲ አማራጮች ታትመው በዛሬው ዕለት ለመድረክ ተሳታፊዎች አንደሚታደል አስታውቀዋል።

በመድረኩ በምርጫ እና ድህረ ምርጫ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች እና የፓርቲው ሚና ምን መሆን እንዳለበት ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

ፓርቲው ለሰላም፣ ለልማትና ቀጣይነት ላለው ሀገራዊ ዕድገት የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲያቸው ለምርጫ ሂደት ዴሞክራሲያዊነት የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም