በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የአፍሪካ ህብረት እና የኮሜሳ የጋራ ልዑክ በዛምቢያ የቅድመ ምርጫ ምልከታ አከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የአፍሪካ ህብረት እና የኮሜሳ የጋራ ልዑክ በዛምቢያ የቅድመ ምርጫ ምልከታ አከናወነ
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የአፍሪካ ህብረት እና የኮሜሳ የጋራ ልዑክ በዛምቢያ የቅድመ ምርጫ ምልከታ አከናውኗል።
የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከሚያዝያ 26 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በዛምቢያ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
በቆይታቸውም ነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው የዛምቢያ አጠቃላይ ምርጫ አስቀድሞ የተሰየመውን የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የጋራ የቅድመ ምርጫ እና የፍላጎት ግምገማ ልዑክን በሊቀመንበርነት መርተዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን እና ከአፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከኮሜሳ የተውጣጣው ልዑክ ከምርጫ እና የመልካም አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክሮችን አድርገዋል።
በውይይቶቹ የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር፣ የዛምቢያ ምርጫ ኮሚሽን፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች፣ የኮሜሳ ዋና ፀሐፊ፣ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
ምክክሩ በዋናነት በዛምቢያ ያለውን የቅድመ ምርጫ ድባብ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማትን ዝግጁነት በመፈተሽ ላይ ያተኮረ ነው።
በተጨማሪም ነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ፣ ግልጽ እና አካታች እንዲሆን እየተከናወኑ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።