በክልሉ በአንድ ወር ውስጥ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻለ የቡና ችግኝ ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በአንድ ወር ውስጥ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻለ የቡና ችግኝ ተሸፍኗል
ዲላ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፈው አንድ ወር ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻለ የቡና ችግኝ መሸፈኑን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነውን ስነ ምህዳር በመጠቀም የቡና ማሳን የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ነው።
በተያዘውም ዓመት ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ አዲስና ያረጀ ቡና እድሳት በሚከናወንበት መሬት ላይ በበልግ እና በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በተሻሻለ የቡና ዝርያ ለመሸፈን ወደተግባር ተገብቷል።
በዚህም ካለፈው የሚያዚያ ወር ጀምሮ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከ40 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተከላ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፈው አንድ ወርም ከ17ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻለ የቡና ችግኝ ተሸፍኗል ያሉት አቶ አማኑኤል፣ ከዚህ ውስጥ ከ5 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የለማ እንደሆነና ይህም በክልሉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህም የክልሉን በሄክታር 10 ኩንታል አማካይ የቡና ምርታማነት በቀጣይ ዓመታት ወደ 12 ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በዞኑ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝርያዎች በኩታ ገጠም የመተካቱ ተግባር ውጤት ማምጣቱን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት በዞኑ ባለፈው ሚያዚያ ወር ብቻ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ 11 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ተከላ ተከናውኗል።
ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬቱ በተደራጁ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲለማ የተደረገ ነው።
በዞኑ ዲላ ዙሪያ ወረዳ የሽገዶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ያቆብ ማሮ በበኩላቸው፤ በማሳቸው የነበረው ቡና በእርጅና ምክንያት ምርት ወደማይሰጥበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እሳቸውን ጨምሮ 75 የአካባቢው አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው በ46 ሄክታር መሬት ላይ ያረጀ ቡና አንስተው በተሻሻለ የቡና ዝርያ መተካታቸውን ተናግረዋል።