የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ መደረጉ ያልተገባ ወጪና እንግልትን አስቀርቷል - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ መደረጉ ያልተገባ ወጪና እንግልትን አስቀርቷል - ተገልጋዮች
ሀዋሳ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንዲሰጡ መደረጉ ያልተገባ ወጪና እንግልትን እንዳስቀረላቸው በሀዋሳ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
ኢዜአ በሀዋሳ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ቀደም ሲል በቀበሌ ይሰጡ የነበሩ የነዋሪነት ማረጋገጫ መታወቂያ፣ የልደት፣ የጋብቻና ሌሎች የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል እያገኙ ነው።
ይህም ያልተገባ ወጪና እንግልትን እንዳስቀረላቸው የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል በሀዋሳ ታቦር ክፍለከተማ ዱሜ ቀበሌ የምትኖረው ወይዘሪት አፎሚያ ወልደሚካኤል እንዳለችው፤ ቀደም ሲል የቀበሌ መታወቂያ፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀትና ሌሎች የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን ከቀበሌ ለማውጣት እንግልት ይደርስባቸው ነበር።
የሲዳማ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ስፍራ ከማግኘት ባለፈ እንግልትና አላስፈላጊ ወጪን እንዳስቀረላቸው ተናግራለች።
አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ በመሆኑ መታወቂያና የልደት ካርድ ለማውጣት የመጣችበትን ጉዳይ በማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቋን ገልጻለች።
ለልጃቸው የልደት ካርድ ለማውጣት እንደመጡ የገለጹት አቶ ለጊዴ ዮታ የተባሉ ሌላው ተገልጋይ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በቀበሌ በሳምንት ለሁለት ቀን ብቻ ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁንና አገልግሎቱን ፈልጎ ወደ ቀበሌ የሚመጣው ሰው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለወረፋ ከመጋለጥ ባለፈ አገልግሎቱን ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ አድርጎት መቆየቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በሁሉም የሥራ ቀናት እያገኙ በመሆኑ ችግሩ ቢፈታም በመስተንግዶ በኩል የሰው ሀይል እጥረት አለ ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ተሰማ እንዳሉት፤ ኤጀንሲው ነዋሪዎችን የመመዝገብ፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የሞትና የልደት ምዝገባ እንዲሁም የቀበሌ መታወቂያ የመስጠት ሥራዎችን ይሰራል።
በክልሉ በሚገኙ አራት የዞን እና በሁሉም የወረዳ ከተሞች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩ ቀደም ሲል በቀበሌና በተለያዩ ተቋማት ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለመስጠት ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከሀይማኖት፣ ከጤና፣ ከዕድሮች እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ኤጀንሲው በትብብር እየሰራ መሆኑን ነው አቶ ታመነ የተናገሩት።
አንድ አገልግሎት ፈላጊ በተለያየ ምክንያት ወደ ኤጀንሲው መምጣት ካልቻለም ቤት ለቤት የፈለገውን አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር ኤጀንሲው መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ ከ110 ሺህ ለሚበልጡ ተገልጋዮች አገልግሎቶችን ለመስጠት ተችሏል።