ቀጥታ፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የበለፀገው "ሀቂላ ላብ" የተሰኘው መተግበሪያ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ እያደረገ ነው

ጅማ ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦በጅማ ዩኒቨርሲቲ የበለፀገው "ሀቂላ ላብ" የተሰኘውና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘው መተግበሪያ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ "2030" ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ መምህራንና ተማሪዎችን ያሳተፉ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያበረከተ ይገኛል። 

ከእነዚህም መካከል በ "ሀቂላ ላብ" ፕሮጀክት ስር የበለጸገውና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘው የጤና መተግበሪያ አንዱ ሲሆን ''ሀቂላ'' የአፋን ኦሮሞ ቃል ሲሆን ጥበብ የሚል ትርጓሜን እንደያዘም ተገልጿል።

በዚሁ ስያሜ የሚታወቀው መተግበሪያ በ2014 ዓ/ም የፖሊዮ በሽታን ለመለየት በሚል ታስቦ የተሰራና አሁን ላይ ግን አምስት ዓይነት በሽታዎችን እንዲለይ ተደርጎ ወደ ትግበራ ገብቷል። 

መተግበሪያው በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቋንቋዎቹን ወደ አምስት የማሳደግ ውጥን እንዳለም ተመልክቷል።

በወቅቱ መተግበሪያው የፅሁፍ መረጃን ብቻ ወስዶ የበሽታውነ ዓይነት እንዲለይ የተሰራ ቢሆንም ኋላ ላይ በተደረገለት ማሻሻያ የፎቶ እና የተንቀሳቃሽ ምስል መረጃን በመጠቀም አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል። 

የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሙሉእመቤት አበራ እንደገለፁት፤ ተቋሙ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ በግብርና፣ በጤና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ከ 140 በላይ ማህበረሰብ ተኮር ምርምሮችን አከናውኗል። 

ይህም የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባሻገር የዕውቀት ሽግግር እንዲሳለጥ የበኩሉን ሚና መወጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም በ "ሀቂላ ላብ" ፕሮጀክት ስር የበለጸገውና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘው የጤና መተግበሪያም በመምህራን እና ተማሪዎች ተሳትፎ እውን ሊሆን መቻሉን አመልክተዋል። 

የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ገላን አያና (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መተግበሪያው መጀመሪያ ላይ የፖሊዮ በሽታን ለመለየት ታስቦ የተሰራ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ ወባንና ኩፍኝን ጨምሮ አምስት ዓይነት በሽታዎችን የመለየት አቅም እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል። 


 

በአሁኑ ወቅት መተግበሪያው በጅማ ከተማ እና በሰቃ ወረዳ በሚገኙ 8 የጤና ተቋማት፣ በሸነን ጊቤ ሆስፒታል እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የህክምና ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። 


 

በሸነን ጊቤ ሆስፒታል የጤና ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ሀሊማ አባተማም፣ መተግበሪያው ስራቸውን በእጅጉ እንዳቀለለላቸው ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም በሽታዎችን ለመለየት ከ30 እስከ 40 ደቂቃዎች ይወስድ እንደነበር ገልጸው የ "ሀቂላ" መተግበሪያን በመጠቀም ወደ10 ደቂቃ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

አገልግሎቱን ከጅማና አካባቢዋ በተጨማሪ ወደ ሌሎች ዞኖች ለማስፋፋት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም