ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት በአርዓያነት የሚወሰድ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት በአርዓያነት የሚወሰድ መሆኑን የዓለም አቀፍ የጤና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ ክትባት ክሊኒካዊ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቋ ለበሽታ ፈጣን ምላሽ ያላትን ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በወረርሽኝ ዝግጁነትና ፈጠራ ጥምረት (CEPI) የዝግጁነትና ምላሽ ዳይሬክተር ዶክተር ኒኮል ሉሪ እና የአፍሪካ ክሊኒካል ምርምር አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቪክቶሪን ኦዊራ  ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዶክተር ኒኮል ሉሪ እንደገለጹት፤ በጤና ዘርፍ ዝግጁነት መሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ ሙያተኛና የአመራር ቁርጠኝነት ለበሽታ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ወሳኝ ጉዳይ ናቸው።

በዚህም የኢትዮጵያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ የተሰናሰለ የአመራር ሥርዓት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤና ዘርፍ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ዝግጁነትም ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት በሁሉም መስክ በአርዓያነት የሚወሰድ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ቀጣይ በሰው ሃብት ልማት፣ የጥናትና ምርምር ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ክሊኒካል ምርምር አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቪክቶሪን ኦዊራ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለማርበርግ ቫይረስ የሰጠችው አፋጣኝ ምላሽና ውጤታማ የክሊኒካል ሙከራ አስደናቂ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ በጤናው ዘርፍ በትብብር የመስራት ፍላጎት እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ ይህም ሀገራት ለበሽታ ምላሽ የሚኖራቸውን አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም