የ1447ኛው የሐጅ ጉዞ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የ1447ኛው የሐጅ ጉዞ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦የ1447ኛው የሐጅ ጉዞ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።
የሐጅ መርሃ-ግብሩን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግቢ ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።
ፕሬዚዳንት ሸህ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት፤ የ1447ኛው የመጀመሪያ ዙር የሐጅ ጉዞ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
የሐጅ ጉዞ ለሚያደርጉ እምነቱ ተከታዮችም የመልካም ጉዞ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
መንግሥት የሐጅ ጉዞን የተሳለጠ ለማድረግ ከምዝገባና ክፍያ ስርዓት ጀምሮ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለሐጅ ተጓዦች ለሚያደርገው የተሳለጠ አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ኃላፊ ለማ ያደቻ፤ አየር መንገዱ የሐጅ ተጓዦችን በማመላለስ ረገድ የረዥም ጊዜ ታሪክ እንዳለው ገልጸዋል።
ዘንድሮም ይህን የረዥም ዘመን አገልግሎት በማላቅ ጉዞውን የተመቸና የተሳለጠ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።