የኢትዮጵያ የተፋሰስና የአካባቢ ጥበቃ ስኬታማ የልማት መርሃ ግብሮች የበለፀገ የደን ሃብት እንዲፈጠር እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የተፋሰስና የአካባቢ ጥበቃ ስኬታማ የልማት መርሃ ግብሮች የበለፀገ የደን ሃብት እንዲፈጠር እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የተፋሰስና የአካባቢ ጥበቃ ስኬታማ የልማት መርሃ ግብሮች የበለፀገ የደን ሃብት እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በተያዘው በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት መርሃ ግብር 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት መልማቱንም አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን፤ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ የፈጠረው የደን መመናመን ከፍተኛ የአካባቢ መራቆትን አስከትሎ ነበር ብለዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የአፈር ለምነትን በመቀነስ በግብርና ምርታማነት፣ በዱር እንስሳትና ዕፅዋት ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት በአረንጓዴ አሻራና የአካባቢ ጥበቃ ልማት መርሃ ግብር የሥነ-ምኅዳር ደኅንነት እንዲያገግም ያስቻለ ስኬታማ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የህብረተሰቡን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትን ባህል በማጎልበት የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን እያስጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመትም በ22ሺህ 59 ተፋሰሶች 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት በተያዘው ዕቅድ፤ እስካሁን 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ ተፋሰስ መልማቱን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ክልሎች የሥነ-ምኅዳር ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ የተፋሰስና የአካባቢ ጥበቃ የልማት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በህብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ ሰፋፊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የልማት ሥራዎችም የተራቆተ የመሬት ገፅታ እንዲያገግም በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን አስረድተዋል።
የህብረተሰቡ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ባህል እያደገ መምጣቱም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም በርካታ ዜጎች በንብ ማነብ፣ እንስሳት መኖ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መርሃ ግብሮች ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህም የህብረተሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ባለቤትነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ በደን ሀብት የበለጸገች ለምለም ሀገር እንድትሆን እያደረጋት መሆኑን አንስተዋል።