በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር እርሻ ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር እርሻ ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል
አምቦ ፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ደጀኔ ደቡሼ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን በ2018/19 የምርት ዘመን 902 ሺህ 892 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዷል።
ከልማቱም ከ34 ነጥብ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም 549 ሺህ 190 ሄክታር መሬት መታረሱን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥም ከ144 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በበቆሎ እና በማሽላ ዘር መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡
በመኸር እርሻ ስራውም ከ300 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን የህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ስርጭት ባለሙያ አቶ ዳኛቸው አለማየሁ በበኩላቸው፣ በዞኑ ለመኸር እርሻ እስካሁን ወደ 548 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የአፈር መዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ መቅረቡንም ተናግረዋል።
በዞኑ የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ሙለታ ጉተማ፤ በመኸር እርሻ ወቅት ተገቢውን ምርት ለማግኘት አንድ ሄክታር ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡ አሰራሮችንና ግብዓቶችን በመጠቀም ጥሩ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
አንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸውን ማሽላ፤ ጤፍና ገብስ ለመዝራት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አበራ ቶሎሳ ናቸው።
አሁን ላይ በበጋ መስኖ ያለሙትን ምርት ሙሉ በሙሉ በማንሳት ወደ መኸሩ እርሻ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
በዞኑ ባለፈው መኸር ከለማው ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ 33 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።