በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 180 ሔክታር መሬት በተለያዩ ችግኞች ይሸፈናል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 180 ሔክታር መሬት በተለያዩ ችግኞች ይሸፈናል
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 180 ሔክታር መሬት በተለያዩ ችግኞች እንደሚሸፈን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የደን ልማት እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክረምቱ ወቅት ለሚከሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር የደን ሽፋንን በመጨመር፣ የደረቁ ምንጮች እንዲያገግሙ በማድረግ እና የግጦሽ መሬት መጠንን በመጨመር አመርቂ ውጤት ተመዝግቦበታል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ 71 ተራሮችን የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በለውጡ አመታት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት 18 ነጥብ 9 ከመቶ የነበረውን የደን ሽፋን ከ 23 ነጥብ 8 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉንም ተናግረዋል።
ይህንን ለማስቀጠልም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በ180 ሔክታር መሬት በተለያዩ ችግኞች ለመሸፈን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም የችግኝ፣የጉድጓድ እና ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች በበቂ ሁኔታ መደረጉን አመልክተው በአሁኑ ወቅትም የበልግ ወቅት የችግኝ ተከላ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የችግኝ ተከላው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አመልክተው ለክረምት ወቅት ተከላ የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተመዘገበውን ለውጥ ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ሊረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።