በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እና ሀገራዊ እድገትን የሚያፋጥኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር ለማቃለል እና ሀገራዊ እድገትን የሚያፋጥኑ ናቸው
ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሚያወጣቸው የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር ከማቃለል ባለፈ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን የሚያግዙ መሆናቸውን አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ 5ኛውን ዓለም ዓቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ እያካሔደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዘርፉን በማጠናከር የአካባቢውን ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች ተግባር ተኮር የምርምር ስራዎችን እያካሄደ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የምርምር ስራዎቹ የማህበረሰቡን ችግር ከማቃለል ባለፈ ሀገራዊ እድገትን በሚያፋጥን አግባብ እንዲተገበሩ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የዩኒቨርስቲው ጥናትና ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሳይ ሙላት (ዶ/ር) በበኩለቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከሀገር ውስጥና ከውጭ የምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሀገር በቀል እውቀቶቸን ጥቅም ላይ ለማዋል የጀመራቸው ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።
በኮንፍረንሱ 27 የምርምር ስራዎች የቀረቡ ሲሆን ተግባራዊ እንዲሆኑም በቅንጅት እንደሚሰራም ነው ያመለከቱት።
በኮንፍረንሱ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የማታው አዲስ (ዶ/ር)፤ ለጤናና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል አዲስ ቴክኖሎጂ ላይ ያደረጉትን የምርምር ስራ አቅርበዋል።
የምርምር ኮንፍረንሶች እርስ በእርስ ትስስር በመፍጠር የምርምር ስራዎችን በቅንጅት ወደ ተግባር ለማሸጋገር እንደሚያግዙም አመልክተዋል።
ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ኢርፖሴ ኢንስኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የምርምር ኮንፍረንሶች የጋራ ሃሳብን በማፍለቅ የሀገርን ኢኮኖሚና ማህበራዊ አቅም ለማሳደግ ያግዛሉ ብለዋል።