ቀጥታ፡

በወሰድነው ካርድ ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል

ሚዛን አማን፤ ግንቦት 1/2018(ኢዜአ)፦ በወሰድነው ካርድ ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ቀን በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሳተፉ በልዩ ሁኔታ ካርድ እንዲያወጡ ምርጫ ቦርድ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህን ዕድል ተጠቅመው ምርጫ ካርድ ያወጡ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በወሰዱት ካርድ ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ካነጋገራቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ አስታውሰኝ አምሃ በምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሳተፍ ገልጾ፣ ምርጫ ቦርድ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ ካርድ እንዲያወጡ ማመቻቸቱ የምርጫውን አሳታፊነት ያሳያል ብሏል።

በዘንድሮ ምርጫ በመሳተፍ ለቀጣይ ሀገርን የሚመራ ፓርቲ መምረጥ የሚያስችለውን ዕድል በማግኘቱ መደሰቱን ገልጾ፣ በምርጫ የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ ስላለው ካርዱን በሚገባ እጠቀምበታለሁ ነው ያለው።

  

ተማሪ ነሲማ ሀሰን በበኩሏ ትምህርታቸው ሳይስተጓጎል በምርጫ የሚሳተፉበት እድል መመቻቸቱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁማ፣  ይህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁሉንም ያሳተፈ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳያል ብላለች። 


 

የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ካርድ ወስደው እየተዘጋጁ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ ተማሪ ሺዘመድ አይቼው እና ወንድማገኝ አምቦ ናቸው።

ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተመቻቸው ዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ተጠቅመው ምርጫ ካርድ እንዳወጡ ገልጸው፣ በጠቅላላ ምርጫው ድምጻቸውን ለፈለጉት ፓርቲ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚጠቀሙ አረጋግጠዋል።  


 

ለእዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሀን እያደረጉት ያለውን ክርክርና የሚያቀርቡትን ማኒፌስቶ በመከታታል እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም