ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከመቻል በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ቡና በ42 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው መቻል በ48 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡናማዎቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፉም። በ30ኛ ሳምንት መቻል ከአዳማ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።

ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

መቻል ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ያደርጋል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ36 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በ30 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች፣ መቀሌ 70 እንደርታ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም።

ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና መቀሌ 70 እንደርታ ደግሞ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ነው።

ሀዲያ ሆሳዕና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሀዲያ ሆሳዕና በ35 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሃዋሳ ከተማ በ44 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።  ቡድኑ ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ሁለቱም ቡድኖች የአሸናፊነትን መንገድ ለማግኘት ይጫወታሉ።

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከምድረ ገነት ሽሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

አዳማ ከተማ በ35 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። ምድረ ገነት ሽሬ በ33 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ባለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው አዳማ ከተማ ሶስት ነጥብ ለማግኘት እና ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ለመራቅ ይጫወታል።

በ30ኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1 ለ 0 ያሸነፈው ምድረ ገነት ሽሬ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት  እስከ ግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና በ55 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በ14 ጎሎች ይመራል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች የሆኑት አዲስ ግደይ እና ናትናኤል ዳንኤል በተመሳሳይ 10 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም