ለዋንጫው የሚፎካከረው ማንችስተር ሲቲ ብሬንትፎርድን ይገጥማል - ኢዜአ አማርኛ
ለዋንጫው የሚፎካከረው ማንችስተር ሲቲ ብሬንትፎርድን ይገጥማል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ማነችስተር ሲቲ ብሬንትፎርድን በኢትሃድ ስታዲየም ያስተናግዳል።
ማንችስተር ሲቲ በ71 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ብሬንትፎርድ በ51 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ35ኛ ሳምንት ከኤቨርተን ጋር ሶስት አቻ በመውጣት የዋንጫ እድሉን በራሱ የመወሰን እድል ያጣው ሲቲ ከመሪው አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ለማድረግ ይጫወታል።
ማንችስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አለው።
በ35ኛ ሳምንት ዌስትሃም ዩናይትድ 3 ለ 0 የረታው ብሬንትፎርድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ተስፋውን ለማለምለም ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሰንደርላንድ ከማንችስተር ዩናይትድ በስታዲየም ኦፍ ላይት ይጫወታሉ።
ሰንደርላንድ በ47 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ማንችስተር ዩናይትድ በ64 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ሰንደርላንድ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።
በ35ኛው ሳምንት ሊቨርፑልን 3 ለ 2 በመርታት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ያረጋገጠው ዩናይትድ፣ ያለውን ጥንካሬ አዝልቆ ለመቀጠል ይፋለማል።
ሊቨርፑል ከቼልሲ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላኛው ተጠቃሽ መርሐ ግብር ነው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በ58 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ቼልሲ በ48 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሊቨርፑል የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የዛሬው ሶስት ነጥብ ያስፈልገዋል።
በአንጻሩ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች የተሸነፈው እና ከሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ውጪ የሆነው ቼልሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ፉልሃም ከቦርንማውዝ፣ ብራይተን ከዎልቭስ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።