ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ስኬታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ስኬታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤዉን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ  አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና  የከተማው ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማብራሪያቸው፤ በመዲናዋ ለህዝብ በተገባው ቃል መሠረት በሁሉም መስክ ዕድገትን የሚያፋጥን የልማት ስኬት መመዝገቡን አብራርተዋል።

ለአብነትም የነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በመንግስት፣ በመንግስትና በግል አጋርነት፣ በሪል እስቴት፣ በግለሰብና በግለሰብ-ግለሰብ አጋርነት በርካታ ቤቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በፕሮጀክት ግንባታ የተፈጠረውን ውጤታማ ስትራቲጂያዊ አፈፃጸም በማጎልበት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በማህበራዊ ዘርፍም በጤና መከላከልና አክሞ ማዳን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የሚያፋጥን ውጤታማ የጤና ተቋማት ግንባታ ዕውን ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል።

በዚህም በነባር ሆስፒታሎች ማስፋፊያና አዳዲስ የጤና ተቋማት ግንባታ የእናቶችና ሕፃናትን ጨምሮ የዜጎች ጤና አገልግሎት ጥራትንና ተደራሽነትን የሚያስጠብቅ መሠረተ ልማት መገንባቱን አንስተዋል።

የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎችም የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ማድረግ ያስቻለ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

በዚህም የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና በቅዳሜና እሁድ ገበያና የገበያ ማዕከላት ሌሎች የምርት አቅርቦት ሥራዎች አቅርቦትና ፍላጎትን ማመጣጠን ያስቻለ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል።


 

የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ በተከናወኑ ተግባራትም በተሽከርካሪ አቅርቦት፣ በመኪና ማቆሚያና በብዙኅን ትራንስፖርት ዘርፍ ወሳኝ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

በመጭው አዲስ ዓመትም 500 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀረቡለትን ልዩ ልዩ ሹመቶችን ያጸደቀ ሲሆን የምክር ቤቱን የፍትሕና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እጩዎች እንዲሁም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባን ሹመት አጽድቋል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ9 ነጥብ 94 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም