ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የስፖርት መሠረተ ልማት ስኬት ዓለም አቀፍ የስፖርት ኹነቶችን የማስተናገድ ዕድል እየፈጠረ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ የስፖርት መሠረተ ልማት ስኬት ዓለም አቀፍ የስፖርት ኹነቶችን የማስተናገድ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ  አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና  የከተማው ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጉዳዮች በሰጡት ማብራሪያ፤ በአዲስ አበባ ለሀገር ተረካቢ ሕፃናትና ወጣቶች ምቹ ምኅዳር መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም በሕፃናት ማቆያና በልጆች መጫወቻ ማዕከላት ግንባታ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ጤናማና ብቁ የሚያደርጉ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቶች የስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህል በማዳበር ጊዜያቸውን በአካልና በአዕምሮ የሚያዳብሩበት ምኅዳር መፍጠር እንደተቻለ አንስተዋል።

በዚህም 495 የነበረውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አሁን  ወደ 2 ሺህ በማሳደግ ጤናማና ብቁ የሆነ ተተኪ ስፖርተኛን በማፍራት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በስፖርት መሰረተ ልማት ማስፋፋትና ለማህበረሰቡ ቅርብ እንዲሆን በማድረግ በተሰራው ስራ ከተማዋን ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች እንድታስተናግድ እያስቻላት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነትም በሚያዝያ ወር ብቻ ሶስት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶች በአዲስ አበባ መስተናገዳቸውን አብራርተዋል።

ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ወድድሮች የሀገራችንን ባህልና ዕሴት በማስተዋወቅ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በመፍጠር በወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

የአቃቂ ዓለም አቀፍ ሜዳ፣ የአደይ አበባ፣ የአዲስ አበባና አበበ ቢቂላ ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች ለመዲናዋ የስፖርታዊ ውድድር አቅም እንደሚሆኑ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም