ኢትዮጵያ ታመርታለች፤ የተሟላ ሉዓላዊነቷን የማረጋገጥ ጉዞዋን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታመርታለች፤ የተሟላ ሉዓላዊነቷን የማረጋገጥ ጉዞዋን አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ታመርታለች፤ የተሟላ ሉዓላዊነቷን የማረጋገጥ ጉዞዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
"ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አራተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ የመዝጊያ መርኃግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በአምራች ኢንዱስትሪው የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች የኢትዮጵያን ብልፅግና ያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ የሀገርን ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለመቀጠል ውድድሩን መምራት ካልሆነም ከዓለም እኩል መራመድ ይገባል ብለዋል።
በዚህ የዓለም ሁኔታ ራሱን የቻለ ያሸንፋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ረገድ አምራች ኢንዱስትሪው ወሳኝ ዓምድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግስት ይሄንኑ በሚገባ በመረዳቱ ከመደመር ፍልስፍና እሳቤ የሚመነጩ፣ የፖሊሲ ነጻነትን የሚያጎናጽፉ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመተግበር ሀገር ከነበረባት ስብራት አገግማ በዓለም አደባባይ ስሟ በበጎ እንዲጠራ እያስቻለ ነው ብለዋል።
የሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት በሙሉነት የሚረጋገጠው በጥራት፣ በዓይነት እና በብዛት የኢንዱስትሪ ምርቶችን በራስ ዕውቀት፣ በራስ ክህሎት እና በራስ ቴክኖሎጂ ማምረት ሲችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ ምቱ እና ትርታው ጤናማ ካልሆነ፣ በኢኮኖሚ ዘርፉም ሆነ በአጠቃላይ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ መዳከምን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
መንግሥት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የታለመውን ዘላቂ ዕድገት እና ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ፣ ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያበረክተውን ድርሻ በፍጥነትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳደግ ፖሊሲዎችን ማሻሻሉን፣ አሠራሮችን መዘርጋቱን፣ የማበረታቻ ሥርዓት መፍጠሩን፣ አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፍ ብሔራዊ ካውንስልም ማቋቋሙን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዚህ ሪፎርም አካል መሆኑን በማንሳት በአራት ዓመታት ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
ከግብዓት አቅርቦት፣ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ከሎጅስቲክስ አገልግሎት፣ ከሰው ኃይል ልማት እና ምቹ የቢዝነስ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር በርካታ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ሆነ በካውንስሉ በተሠሩ ሥራዎች የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሻሻል ተችሏል ብለዋል፡፡
ተኪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት መጀመሩ ከወጪ ንግድ እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻርም ብዙ ለውጦች መምጣታቸውን ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሥራ ባህልንና ምርታማነትን ማሻሻሉን፣ የሀገር ውስጥ ምርትን የመሸመት እና የመጠቀም ባህልን ማሳደጉንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አምራች ኢንዱስትሪው ከራሱ ዘርፍ ዕድገት ባሻገር እንደ ግብርና፣ ኮንስትራክሽን፣ ቱሪዝም እና ጤና ላሉ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ዘርፎች መነቃቃት እያደረገ ያለው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪውን ከዚህ በላይ ለማሳደግ ኢንዱስትሪያዊ አመለካከት፤ ኢንዱስትሪያዊ ባለ ሀብት እና ኢንዱስትሪያዊ አመራር መኖር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ጎንበስ ብሎ አፈር ነክቶ ከብረትና ከማዕድናት ጋር ታግሎ፣ ታሪክን መቀየር ያልተቻለው በዚህ የአመለካከት መዛነፍ የተነሣ ነው በማለት አሁን እሱን እየቀየርን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት ኤክስፖ የላቁ አዳዲስ እና የተሻሻሉ ምርቶች እንደሚቀርቡም ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም የማምረትና የተሟላ ሉዓላዊነቷን የማረጋገጥ ጉዞዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል በአፅንኦት ተናግረዋል።