ቀጥታ፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት የቴክኖሎጂ አሰራር ቀልጣፋና የፍትሕ ተደራሽነትን የሚያጠናክር መሆን አለበት

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦የጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት የቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓት ቀልጣፋና የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያጠናክሩ መሆን እንዳለበት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የበጀት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት የበጀት ፍላጎትን አስመልክቶ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የ2018 የዘጠኝ ወራት የበጀት አፈጻጸም፣ የበጀት ጣሪያና ማስተካከያዎች ጋር የተያያዙ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የፍርድ ቤቶች በጀት የሚሰጡ አገልግሎቶችንና ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ከማድረግ አኳያ ለውጦች መኖራቸውን ገልጸዋል።


 

የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትና ግብዓት በማሟላት የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትን የሚያስጠብቅ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በበጀት አጠቃቀም ሥርዓትም በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የተቋሙን በጀት በአግባቡ መጠቀም መቻሉን አንስተዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ለሊሴ ደሳለኝ፤ የዳኝነት አገልግሎትን ቀልጣፋና ግልጽነት የሚያስጠብቅ ውጤታማ የተቋም ማሻሻያና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቡላ ዋጋሪ፤ የዳኞችን የመኖሪያ ከባቢ፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማስተካከያ መደረጉን አንስተዋል። 

ለዳኞች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠርና የደመወዝና ጥቅማጥቅም ማስተካከያ ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ የበጀት ማስተካከያ ማስፈለጉን ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ኪያር፤ የዳኞችን የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማስተካከያ መደረጉ የበጀት ማሻሻያ እንዲደረግ ያስቻለ ዐበይት ተግባራት መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪአ ፍርድ ቤት የአስተዳደርና የሰው ሀብት ዋና ዳይሬክተር አየለ ዳሮርሳ፤ በዲጂታልና የሕንጻ ዕድሳት ሥራ የተቋምን ምቹ የሥራ ከባቢ የሚያላብስ ምኅዳር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ፤ የፍርድ ቤቶች የበጀት አፈፃጸምና ማስተካከያ መረጃ ግልጽነት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቶች የችሎት ማስቻያ ሕንጻዎችን ጥገና በመደበኛ በጀት በማከናወን ለማጠናቀቅ የበጀት እጥረት እንዳይፈጠር ጥናቶችን በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት የቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓት ቀልጣፋና የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያጠናክሩ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም