ቀጥታ፡

ነጻነት እና ህግን አጣምሮ መስራት ያስፈልጋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የሚዲያ ተቋማት ነጻነት እና ህግን አጣምረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት "የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ የሚዲያ ተቋማት የምክክር መድረክ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተሳታፊች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ በለውጡ ማግስት በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን መፍታት የመጀመርያ እርምጃ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም ብሎጎች እንዲከፈቱ እና በኢትዮጵያ የሚዲያ ጃሚንግ ስርዓት እንዲቀር መደረጉን አብራርተዋል፡፡

አሳሪ ህጎች በተለይም የፀረ ሽብር ህጉ ለመናገር እድል የሚሰጥ እንዳልነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም እንዲሻሻል መደረጉን አውስተዋል፡፡

በሪፎርሙ የነበረው ሚዲያን የመክፈት እና ሁሉም ሃሳብ ካለከልካይ እንዲንሸራሸር ማድረግ ቀላል እንዳልነበርም ተናግረዋል፡፡

የሚዲያውን መከፈት ተከትሎ ነጻነትን ማስተዳደር የተሳናቸው ሚዲያዎች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያዎች ምን መምሰል እንዳለባቸው ለተጠየቁት ጥያቄም በሰጡት ማብራሪያ፤ ሚዲያዎች እውነትን የሚገልጡ እና የጋራ መግባባትን የሚፈጥሩ መሆን እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም በውይይት የሚያምኑ እና ሀገራዊ ግቦች ላይ አውቀው የሚሰሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ነጻነትን ማስተዳደር እና በህግና በስርዓት የመስራት ልምምድ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ርዕሰ ጉዳይ መሸጥ የኢትዮጵያ ሚዲያ አንዱ ስንክሳር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ነጻነትን እና ህግን አጣምሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም