ቀጥታ፡

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ57 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ስምምነት ተፈጽሟል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦በዘንድሮው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ57 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ስምምነት መፈጸሙን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

"ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው የ2018 የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ የመዝጊያ መርኃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ራሷን መቻሏ የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል። 

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለምርታማነትና ለፈጠራ መጠቀም መጪውን ዘመን መዋጀት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአብነት ያህል በአምስቱም ዘርፎች ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ጀማሪ ድርጅቶችን ለማበረታታት በተደረገው ድጋፍ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

በዚህ መርሃ ግብር 20 ስታርት አፖች የፈጠራ ስራቸውን ለጎብኚዎች ማቅረባቸውንም አክለዋል፡፡

አዳዲስ ፈጠራ የተጨመረባቸው የምርት ልማት ውድድሮች በ22 ኢንዱስትሪዎች ለእይታ መቅረባቸውን ጠቅሰው፤ በምግብ ቅምሻ 10 ድርጅቶች ከተለያዩ ግብዓቶች ያመረቷቸውን ልዩ ልዩ ምርቶች በተሳታፊዎች ማስመረጣቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከኤክስፖው ከ12 ሺህ በላይ የግብይት ትስስሮች በአምራቾች መካከል መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 

በ16 የመንግስት ተቋማትና አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል በተደረገ ትስስር ከ57 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ስምምነት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

መንግሥት ለአምራች ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በኤክስፖው ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።

አምራቾች ወደ አፍሪካ ገበያዎች ጭምር መግባት እንዳለባቸው አቅጣጫ የተቀመጠበት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻል ውሳኔ ላይ የተደረሰበት እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ የምርት ሂደትን ለመጀመር መነሳሳት የተፈጠረበት ኤክስፖ ነው ብለዋል።

በርካታ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁና ከከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ መደረጉንም ገልጸዋል። 

የቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከግንቦት 5 እስከ 10 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም