ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንዋን አነጋገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንዋን አነጋገሩ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንዋን አነጋገሩ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንዋ የተመራ ከፍተኛ የሥራ አማካሪ ቦርድ አባላት ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊው የሚመሩት ከፍተኛ የሥራ አማካሪ ቦርድ አባላት በአዲስ አበባ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ ዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) አፈጻጸምን በአህጉራዊ ደረጃ ያለበትን ሁኔታ ለመገምገም መሆኑ ነው የተገለጸው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንዋ ከፕሬዝዳንት ታዬ ጋር ከተወያዩ በኋላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የነበራቸው ውይይት ውጤታማ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው አስደናቂ እድገትና የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ መለወጡ እጅግ አበረታች መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ስኬታማ የልማት ጎዳና ላይ መሆኗን የተናገሩት ምክትል ዋና ጸሐፊው፤ ይህ መልካም ተሞክሮም በዓለም አቀፍ መድረክ ቀርቦ በማደግ ላሉ ሀገራት እንደ ትልቅ ትምህርት ሊያገለግል እንደሚችል አስገንዝበዋል።
የ2030 አጀንዳን ለማፋጠንና ከ2030 በኋላ ያለውን ዓለም አቀፍ የልማት ግብ ለመቅረጽ ከአፍሪካ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ውይይት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ስኬታማነት ከመጀመሪያው ጀምሮ ቁልፍ ሚና አላት።
ኢትዮጵያ ሂደቱን ከመጀመሪያው ጀምሮ ስትደግፍ መቆየቷን ጠቁመው፤ እ.ኤ.አ. በ2015 ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ጉባኤ የተካሄደው አዲስ አበባ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት ቡድኑን እጅግ ማስደመሙንም ገልጸዋል።
ለተመዘገበው ስኬትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፕሬዝዳንቱ አመራር ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል።