ቀጥታ፡

የጤና ነገር …

በዮሐንስ ደርበው

የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን ምንድነው?

ሕጻናት ከተወለዱ እስከ 28 ቀናት ባለው ጊዜ በደማቸው ውስጥ ባክቴሪያ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሲዛመት የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን ተብሎ እንደሚጠራ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን ምንነት፣ መንስዔና አጋላጭ ምክንያቶችን በተመለከተ የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አበበ የኔዋ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።


✍️ የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን መንስዔ ምንድን ነው?

የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን የሚመጣው በአብዛኛው በባክቴሪያዎች መሆኑን የገለጹት ዶክተር አበበ፤ ከእነዚህ ባክቴሪያዎች መካከልም በዋናነት Escherichia coli, Group B streptococcus እና Listeria monocytogenes የተሰኙት እንደሚገኙበት ለማሳያነት ጠቅሰዋል።


✍️ ለጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን የሚያጋልጡ ምክንያቶች ይታወቃሉ?

የእንሽርት ውኃ ከምጥ 18 ሠዓት እና ከዛ በላይ ቀድሞ መፍሰስ (prolonged premature rupture of membrane)፤ የመውለጃ ጊዜያቸው በተቃረበበት ወቅት የሚከሰት የእናቶች ኢንፌክሽን (chorioamnionitis፣ Urinary tract infection)፤ የተራዘመ ምጥ (prolonged labor)፤ በቂ የእርግዝና ክትትል አለመኖርና ከጤና ተቋም ውጭ (በቤታቸው) መውለድ ወ.ዘ.ተ. እንደ ኢንፌክሽን አጋላጭ ተደርገው ይጠቀሳሉ ብለዋል ዶክተር አበበ።


✍️ የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽንን መከላከል ይቻላል?

የሕክምና ባለሙያው እንዳሉት፤ የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽንን ለመከላከል በዋናነት አጋላጭ ምክንያቶችን በመለየት እነሱ ላይ ቀድሞ መሥራት ነው።

በዚህም መሠረት፤ ምጥ ሳይኖር የእንሽርት ውኃ ቀድሞ ከፈሰሰ ቶሎ በሐኪም መታየት እና ሕክምና ማድረግ፣ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የእናቶች ኢንፌክሽን (የማህፀን፣ የሽንት ቱቦ፣ የሳንባ ካለ) በአግባቡ መታከም፣ የተራዘመ ምጥ ማስወገድ፣ በቂ የእርግዝና ክትትል ማድረግና በጤና ተቋም መውለድ እንደሚገባ መክረው፤ ይህም ህመሙን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚረዳ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ከተወለዱ በኋላ በአራስ ቤታቸው እያሉ ሳል ወይም ሌላ ተላላፊ ህመም ያለበት ሰው እንዳይቀርብ ማድረግና መጠንቀቅ፣ በቤት ውስጥ ጭስ እንዳይኖር ማድረግ እንዲሁም የጨቅላ ሕጻናት አደገኛ ምልክቶችን በየጊዜው መከታተል ያስፈልጋል ሲሉ መክረዋል።

የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን ምልክቶችን ያሳየ ጨቅላ ሕጻን በቶሎ ወደ ጤና ተቋም ከተወሰደና በተገቢው ሁኔታ ከታከመ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።


✍️ የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን ምልክቶች በውል ይታወቃሉ?

የጨቅላ ሕጻናት ምልክቶች አደገኛ ተብለው እንደሚጠሩ የገለጹት ዶ/ር አበበ፤ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ ረጅም ሠዓት የሚቆይ ማቃሰት፣ የሰውነት ትኩሳት (መቀዝቀዝ)፣ የሰውነት መንቀጥቀጥ፣ ጡት አለመሳብ፣ መፍዘዝና አለመንቃት፣ ራስን መሳት፣ በጣም ተከታታይና ኃይለኛ ትውከት፣ የዐይንና የሰውነት ቢጫ መሆን፣ የሆድ ከመጠን በላይ መወጠር፣ የከንፈርና የምላስ መጥቆር ከምልክቶቹ መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።


✍️ የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን እንዴት ይታከማል?

እንደ ዶ/ር አበበ ገለጻ፤ ከላይ የተጠቀሱት አደገኛ ምልክቶች ከታዩ በቶሎ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ ያስፈልጋል።

በሕክምና ወቅትም፤ የአተነፋፈስ ሁኔታ ታይቶ ለአተነፋፈሱ እገዛ (ኦክስጅን) ሊሰጥ ይችላል ብለዋል።

ትኩሳት ካለም የትኩሳት ማስታገሻ፣ የሰውነት ሙቀቱ ዝቅ ያለ ከሆነ በማሞቂያ (Radiant warmer) እንዲስተካከል ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።

የስኳር መጠናቸው ዝቅ ካለም ግሉኮስ (dextrose) እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።

ከደም የሚወሰዱ ምርመራዎች እና ከጀርባ የሚወሰድ ምርመራ (Cerebro spinal fluid analysis & Culture) ማድረግም እንደ ህመሙ ዓይነት የሕክምናው አካል መሆኑን ነው ያስረዱት።

በዋናነትም በመርፌ የሚሰጡ ፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶችን እንዲወስዱ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም