በኤክስፖው የቀረቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማየታችን በራሳችን የመተማመን መንፈስና መነሳሳትን ፈጥሮብናል - ኢዜአ አማርኛ
በኤክስፖው የቀረቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማየታችን በራሳችን የመተማመን መንፈስና መነሳሳትን ፈጥሮብናል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦በአራተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የቀረቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማየታችን በራሳችን የመተማመን መንፈስና ለቀጣይ ሥራ መነሳሳትን ፈጥሮብናል ሲሉ ኤክስፖውን የጎበኙ ተማሪዎች ገለጹ፡፡
"ኢትዮጵያ ታምርት፤ ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሐሳብ ላለፉት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አራተኛው አገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ኤክስፖም በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
ከተለያዩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎች ኤክስፖውን የጎበኙ ሲሆን፤ ጉብኝቱ ለተማሪዎች ትልቅ የተስፋና የ"ይቻላል" መንፈስን ያሰረጸ ነው፡፡
በዚሁ ጊዜ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተማሪዎች፤ በኤክስፖው የተመለከቷቸው የፈጠራ ስራዎችና ምርቶች ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠሩባቸው ገልጸዋል።
ተማሪ ሮዛ ሃዱሽ እንዳለችውም ኢትዮጵያ ሌሎች አገራት የሚያመርቱትን ምርቶች ማምረት እንደምትችል በተግባር በማየቷ መደሰቷን ገልጻለች፡፡
ይህም " እኛ በቀጣይ በዘርፉ ተሰማርተን የአገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንድንሰራ የ'ይቻላል' መንፈስ ፈጥሮብናል" ብላለች።
ተማሪ ራፍኤል በፍቃዱ እና ተማሪ ቡአዝ አዋድ በበኩላቸው፤ አገራቸው ምርቶችን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ እዚሁ አምርታ ወደ ውጭ መላክ እንደጀመረች መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ይህም አገራዊ አቅም እያደገ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የተመረቱ በርካታ ውጤቶችን በመመልከቷ ኩራት እንደተሰማት የገለጸችው ተማሪ ዮሳን ዳንኤል፤ "ይህ ጉብኝት በቀጣይ በርትተን በመማር የተሻለ ስራ እንድንሰራ የሚያነሳሳን ነው" ስትል ተናግራለች።
በዳይመንድ አካዳሚ የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ኃላፊ መምህር ፋንታ ጌታው በበኩላቸው፤ ኤክስፖው ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን እየተከናወነ ያለውን ስራ የሚያሳይ በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ይህንን መመልከታቸው የነገ አገር ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን፣ ራሳቸውን ለተሻለ ስራ እንዲያዘጋጁ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆናቸው አስረድተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ እንደገለጹት፤ ወጣቶች ኤክስፖውን መጎብኘታቸው በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን አውቀው እንዲጠቀሙና የኢንዱስትሪ ባህል እንዲገነቡ ያስችላል።
"የዛሬ ተማሪዎች የነገዋ የአገር ተረካቢዎች በመሆናቸው፣ የነገ ተልእኳቸውን ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር እያስተሳሰሩ እንዲሄዱ ያግዛቸዋል" ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።