ቀጥታ፡

በክልሉ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል

ቦንጋ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሴቶች ፌደሬሽን አስታወቀ።

ፌደሬሽኑ ከክልሉ አራት ዞኖች ለተወጣጡ የምርጫ ታዛቢ ሴቶች ዛሬ በቦንጋ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።


 

ስልጠናውን የሰጡት የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትዕግስት ወርቁ እንደገለጹት፤ ለምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ፌደሬሽኑ የበኩሉን ለመወጣት አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።  

በቀጣይም ሴቶች በነቂስ ወጥተው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ እንዲመርጡ የማስተማርና የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ 46 ሴቶች ለምርጫ ታዛቢነት በፌደሬሽኑ ተመልምለው የአቅም ግንባታ ስልጠና በተለያዩ ከተሞች እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ከአራት የክልሉ ዞኖች ለተወጣጡ ሴት የምርጫ ታዛቢዎች በቦንጋ ከተማ የተሰጠው ስልጠናም የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሰልጣኞችም ባገኙት ግንዛቤ መሰረት የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ከሸካ ዞን የመጡት ወይዘሮ ፍሬሕይወት ሻረው ናቸው።

ከካፋ ዞን እና ከቤንች ሸኮ ዞን የመጡት ወይዘሮ የምስራች ካሳ እና ወይዘሮ አስማረች ሀይሌ፤ የተጣለባቸውን የታዛቢነት ሚና በብቃት በመወጣት ለምርጫው ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ስልጠናው የነበረባቸውን የግንዛቤ ክፍተት የሞላና ለቀጣይ ሥራቸውም አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም