ቀጥታ፡

ኤክስፖው ምርቶቻችንን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ዕድል ፈጥሮልናል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦አራተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ገለጹ።

"ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ የቆየው የ4ኛው "ኢትዮጵያ ታምርት" ኤክስፖ የማጠቃለያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡ 

ኤክስፖው በከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በተማሪዎች እንዲሁም በመዲናዋ ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት ተጎብኝቷል። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው በኤክስፖው የተሳተፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች፤ መድረኩ የተሻለ የገበያ ዕድልና የምርት ትስስር እንዳመጣላቸው ገልጸዋል። 

የኢ.ዜድ.ኤም ትሬዲንግ ኢንቨስትመንት የማርኬቲንግ ባለሙያ አቶ ቢኒያም ተስፋዬ፤ ድርጅታቸው በፕላስቲክ ፓይፕ ምርት ተሰማርቶ ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን መተካት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ኤክስፖው የሀገር ውስጥ ምርትን በማበረታታት ረገድ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

የዳግም ኬኔዲ ማሽነሪዎች ማምረቻ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማዬ ወልደገብርኤል በበኩላቸው፤ ፋብሪካቸው ከትራንስፎርመር ጀምሮ የተለያዩ የግብርና መሣሪያዎችን በማምረት ለሀገሪቱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን የላቀ ጠቀሜታ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ኤክስፖው ኢትዮጵያ ማምረት እንደምትችል በተግባር ያሳየችበትና ለአምራቾች የሚፈለገውን ግብዓት በቀላሉ ለማግኘት የረዳቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የሆራይዘን አዲስ ጎማ ማኑፋክቸሪንግ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌቱ አብዲሳ፤ ድርጅታቸው ለተለያዩ ተሽከርካሪዎች የሚሆኑ ጎማዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ድርጅቱ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አክለዋል።

በኤክስፖው ላይ የተገኙ ሸማቾች በበኩላቸው፤ የተመለከቷቸው የሀገር ውስጥ ምርቶች የ"ይቻላል" መንፈስን ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሚፈልጓቸውን ምርቶች ከአምራቾች በቀጥታና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፤ በኤክስፖው ላይ ከ300 በላይ ኢንተርፕራይዞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል። 

ኤክስፖው አምራቾች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና ጠንካራ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ትልቅ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።

መንግስት ኢትዮጵያን የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል በማድረግ የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ ለሚሰራው ስራ ይህ ኤክስፖ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ሸማቾችም ምርቶችን በቀጥታ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም