ቀጥታ፡

ሩዋንዳ የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ትሮፊ የዞን 5 ውድድር አሸናፊ ሆነች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን (IHF) ትሮፊ 2026 የዞን 5 የምስራቅ አፍሪካ ውድድር በሩዋንዳ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሁለቱም የዕድሜ እርከኖች ማለትም ከ20 ዓመት እና ከ18 ዓመት በታች በተደረጉት ጨዋታዎች ሩዋንዳ የበላይነቱን በመያዝ የሁለቱም ምድብ ሻምፒዮን መሆን ችላለች።

ከ20 ዓመት በታች የፍጻሜ ጨዋታ፣ ሩዋንዳ አስተናጋጇን ኢትዮጵያን አስተናግዳለች።

ጨዋታው እጅግ ተቀራራቢና በፉክክር የታጀበ የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻም ሩዋንዳ 39 ለ 37 በሆነ ጠባብ የግብ ልዩነት ኢትዮጵያን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

በዚህ የምድብ ፉክክር ኬንያ የሦስተኛነት ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

በተመሳሳይ በ18 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ሩዋንዳ የብሩንዲ አቻዋን በማሸነፍ ሁለተኛ ድሏን አስመዝግባለች።

ለሦስተኛ ደረጃ በኬንያ እና በዩጋንዳ መካከል በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ኬንያ ድል ቀንቷታል። ይህ ውጤት ሩዋንዳ በሁለቱም የዕድሜ ዘርፎች የቀጣናው ቁንጮ መሆኗን ያረጋገጠችበት ሆኗል።

በአጠቃላይ ከሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው ውድድር ላይ ስምንት ሀገራት ተሳትፈዋል።

በዚህም መሰረት አሸናፊዋ ሩዋንዳ በቀጣይ በሚካሄደው የአፍሪካ አህጉራዊ የእጅ ኳስ ውድድር ላይ ቀጣናውን ወክላ እንደምትሳተፍ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም