በኢትዮጵያ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ህግ መኖር ለሀገራዊ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ መሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ህግ መኖር ለሀገራዊ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ መሰረት ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ህግ መኖር የሀገርን ቁልፍ መሰረተ ልማቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ መሰረት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ።
ቋሚ ኮሚቴው የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
ምክትል ሰብሳቢው ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት መሰረተ ልማቶችን ከጥቃት በመከላከል ረገድ ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት እንዳይጎዳ ለማድረግ ያስችላል።
ረቂቅ አዋጁ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ለይቶ ያካተተ መሆኑን አንስተው፤ ተቋማቱ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ በመሆናቸው ለሳይበር ጥቃት እንዳይጋለጡ በማድረግ ረገድ አዋጁ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
ሰብሳቢው አክለውም፣ አዋጁ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውና ብሄራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የሀገሪቷን መሰረተ ልማቶች ከመጠበቅ አኳያ በርካታ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችንና ደንቦችን እየተገበረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፣ በጋራ መስራት በዘርፉ ውጤታማነትን እንደሚያረጋግጥ አመልክተዋል።
ዲጂታል ኢኮኖሚን በስፋት መጠቀም በሚገባን ልክ ሊከተሉ የሚችሉ ስጋቶችን ለመከላከልና ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ እንዲሁም ለቁልፍ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አዋጁ ትልቅ ዕድል ይዞ እንደሚመጣም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ረቂቅ አዋጁ የሀገሪቷን ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለተግባራዊነቱ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዘርፉ በቂና ብቁ ባለሙያዎችን የማፍራት እንዲሁም መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ የመስራት አስፈላጊነት ላይ አስተያየታቸውንና ማብራሪያ የሚሹ ነጥቦችን አቅርበዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ትዕግስት ሀሚድ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለሳይበር ደህንነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በዘርፉ በቂ የሰው ኃይል እየፈራ መሆኑን አንስተው፣ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) በማጠቃለያቸው፤ አስተማማኝ የሳይበር ደህንነትን በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ ከመድረኩ የተገኙ ጠቃሚ ግብዓቶችን በመጠቀም አዋጁን ለተግባራዊነት ለማዘጋጀት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።