ለአጀንዳ 2063 ስኬት የይዘት አመንጭዎች ነፃነትና የሕግ ማዕቀፍ ይሻሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለአጀንዳ 2063 ስኬት የይዘት አመንጭዎች ነፃነትና የሕግ ማዕቀፍ ይሻሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ የይዘት አመንጭዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለአጀንዳ 2063 ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ በነፃነት የሚሰሩበት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልጋቸው የፓናል ውይይት አቅራቢዎች ገለጹ።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ /pulse of Africa/ ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመጀመሪያው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ኃላፊነት የሚሰማቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጠናከር፣ ትብብርን ለመፍጠርና የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግብን ማሳካት የሚያስችል ትብብር መፍጠር ያለመ ነው።
የማህበራዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አፍሪካ የራሷን ትርክት በራሷ ለመገንባት፣ በአሕጉሪቱ ላይ እምነት የሚያሳድጉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ፣ የአፍሪካን መለያ ለመፍጠር የጋራ ምክክር ይደረግበታል።
በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ በረከት ድሪባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የሕብረቱ ምስረታ 100ኛ ዓመት ማብሰሪያ የአፍሪካውያን የ50 ዓመት ዕቅድ ነው።
የአፍሪካ የምትፈልገውን ለመሆን አባል ሀገራት የህብረቱ አጀንዳዎችን በፖሊሲያቸው አካል በማድረግ መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የሕብረቱን የዲጂታል አጀንዳ እውን በማድረግ ረገድ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ የዲጂታል ሽግግር ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችል ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ገልጸው፤ በርካታ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ትኩረት ሰጥታ መስራቷን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የህዝብ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መጀመሯን ገልጸው፣ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት በምሳሌነት ይጠቀሳል ብለዋል።
ምህዳሩ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችን አቅም አሳድጓል ያሉት አቶ በረከት፤ ይህም የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግቦችን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለዲጂታል ይዘት ፈጠራና የይዘት አመንጪዎች ምቹ ምህዳር ፈጥራለችም ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የስትራቴጂና ተደራሽነት ዳይሬክተር ቦቶ ከባቦንዬ ባየንዲ፤ አጀንዳ 2063 የሕብረቱ የ50 ዓመት መሪ ዕቅድ አፍሪካ የምትፈልገውን የምትሆንበት ፍኖት መሆኑን ገልጸዋል።
አጀንዳ 2063 የተቀናጀች፣ ሰላማዊና የበለጸገች አህጉር የመፍጠር ግብ እንዳለው በመግለጽ፣ ለስኬቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ተጠያቂነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የዳጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በሁሉም አባል ሀገራት እንዲተገበር እንፈልጋለን ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ለይዘት ፈጣሪዎች ምቹ የፖሊሲና አሰራር በመዘርጋት ሁሉን አቀፍ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግ ባለሙያ አሻግሬ አብዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እውቀትና ሀሳብ አመንጪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ለይዘት አመንጪዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ምቹ ህጋዊ የአሰራር ማዕቀፍ በመዘርጋት ከጫና ነፃ ሆነው የሚሰሩበትን ዕድል መፍጠር ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ወጣቶች የዲጂታል ዘመን አቀንቃኞች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የሀገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ የሚሰሩበት መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ስኬት በወጣቶች ላይ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ የተፅዕኖ ፈጣሪዎችና ይዘት አመንጪዎችም ሀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።