ቀጥታ፡

የምርጫ ሂደቱ በሃሳብ የበላይነት የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት እያኖረ ነው

ጅማ ፤ ሚያዝያ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የምርጫ ሂደቱ በፖሊሲ ክርክር በሃሳብ የበላይነት የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት እያኖረ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈውበት በተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በርከት ያሉ የክርክር መድረኮች እየተካሄዱበትና የምረጡኝ ቅስቀሳ እየተከናወነበት ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ 50 ሚሊየን 514 ሺህ 155 መራጮች መመዝገባቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ለምርጫው  በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሠማሩ 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መሰጠቱንም የቦርዱ መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ መሰረት የምርጫ ሂደቱ የቀጠለ ሲሆን የድምጽ መስጫው እለትም ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን ቦርዱ ያወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል። 

በምርጫ ሂደቱ እስካሁን ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን አነጋግሯል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስነ-አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ፍቃዱ ቶለሳ (ዶ/ር)፤ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፤ የሂደትና ቀጣይነት ያለው ልምምድ ውጤት ስለመሆኑ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ስርአት እየተፈጠረና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መልካም ጅምር እየታየበት መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት የዘንድሮው የምርጫ ሂደት በፖሊሲ ክርክር በሃሳብ የበላይነት የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ጥሩ መሰረት እያኖረ መሆኑን ለመመልከት ችለናል ብለዋል።

በምርጫው ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃሳብ ክርክር እንዳለ ሆኖ በምርጫው መብትን ለመጠቀም ዜጎች በምርጫ ምዝገባ ያሳዩት ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለማጽናት የሚያስችል መሆኑን አንስተው ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትብብርና ተሳትፎው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።


 

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ሀይለማርያም፤ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት በህዝብ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ የመንግስት ምስረታ የሚካሄድበት የዴሞክራሲ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዚህ አንፃር የዘንድሮው ምርጫ ሂደት እስካሁን መልካም የሚባል የፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣ የዜጎች ተሳትፎና የሲቪል ማህበራት ጠንካራ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም